ትናንት በአዲስ አበባ የነበራቸውን ዝግጅት ጨርሰው ወደ ባህር ዳር የተጓዙት የኢትዮጵያ ከ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባላት ዛሬ ልምምድ አከናውነዋል።
በአቫንቲ ሆቴል መቀመጫውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ ከቀኑ 9 ሰዓት በቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ ላይ ልምምዱን የሰራ ሲሆን ቀለል ያለ ልምምድ እንዲሁም ከሁለት ተከፍለው በግማሽ ሜዳ ጨዋታ በማድረግ አከናውነዋል።
በዛሬው ልምምድ ላይ ጥሪ የተደረገለት ረመዳን የሱፍ የተገኘ ሲሆን የመጀመሪያ መሐል ባልገባ ከሠራ በኋላ የመጀመሪያ ቀን ከመሆኑ አንፃር ቀጣዮቹን ሥራዎች አልሰራም። ሌላኛው በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ ያልሰራው መስፍን ታፈሰ ሲሆን ሜዳ ላይ ከሌሎት አባላት ተነጥሎ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ታይቷል ።
ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል 20 ተጫዋቾች ልምምድ የሰሩ ሲሆን ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ ከቡድኑ ጋር ሲሰራ አልተመለከትነውም። የፖስፖርት ጉዳይ በማስጨረስ ላይ ስለሆነ እንዳልተገኘ እና ነገ ሊቀላቀል እንደሚችል ታውቋል።
የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር የፊታችን ቅዳሜ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚጀመር ሲሆን ኢትዮጵያም ከኤርትራ እና ቡሩንዲ ጋር በምድብ ለ ተደልድላለች።