ቅዳሜ ሐምሌ 10 እንደሚጀመር ሲነገር የነበረው የሴካፋ ውድድር በአንድ ቀን መገፋቱ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ የምታስተናግደው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከሰኔ 26 ጀምሮ እንደሚካሄድ ቀድሞ ቢገለፅም የተሳታፊ ሀገራት በሌላ ውድድር ላይ መሳተፍ የመጀመሪያው ቀኑ ለሁለት ሳምንት እንዲገፋ አድርጎታል። በዚህም ውድድሩ ከሐምሌ 10 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጾ ነበር። አሁን ሴካፋ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን “አንዳንድ አባል ሀገራት በጠየቁት ጥያቄ መሠረት” በሚል ቅዳሜ የሚጀመረው ውድድር ወደ እሁድ እንዲገፋ መልዕክት አስተላልፏል። ስለሆነም ከቅዳሜ ጀምሮ የሚደረጉት የውድድሩ ጨዋታዎች በአንድ ቀን ተገፍተው ከእሁድ ጀምሮ ይደረጋሉ።
በዚህም መሠረት የውድድሩ የመክፈቻ መርሐ-ግብር በምድብ ሀ በሚገኙት ዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል 8 ሰዓት ሲደረግ በምድብ ሁለት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በ10 ሰዓት የምትጫወት ይሆናል።