ዘጠኝ ሀገራትን የሚያሳትፈው የሴካፋ ውድድር የቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት እንደሚያገኝ ተገልጿል።
ስምንት የቀጠናው እና አንድ ተጋባዥ ሀገራትን ተሳታፊ የሚያደርገው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር (ሴካፋ) የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ በትናንትናው ዕለት መከናወኑ ይታወቃል። በውድድሩ ላይ 25 ሺ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ቢታወቅም በየቤታቸው የሚገኙ ደጋፊዎች ጨዋታዎችን በቀጥታ የሚመለከቱበትን አማራጭ ሲጠይቁ ከርመዋል። እርግጥ የሴካፋ ውድድርን የማስተላለፍ መብት ያለው አዛም ቲቪ ቢሆንም ተቋሙ ወደ ባህር ዳር መጥቶ ግዜያዊ ስቱዲዮውን በመገንባት ጨዋታዎችን ማስተላለፉ ማረጋገጫ አላገኘም ነበር።
አሁን በተገኘ መረጃ ግን መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገው አዛም ቲቪ ሁሉንም ጨዋታዎች በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ለማወቅ ተችሏል። በተያያዘ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬት በአማራ ቲቪ አማራጩ የኢትዮጵያን ጨዋታዎች ለማስተላለፍ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገልጾልናል። ተቋሙም የዋልያዎቹን ጨዋታዎች የማስተላለፍ መብት እንዲሰጠው ለአዛም ቲቪ ጥያቄ ማቅረቡን እና እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠው ተረድተናል። ምናልባት ባለመብቱ አዛም ቲቪ እና አማራ ሚዲያ ኮርፖሬት የተባሉትን ጨዋታዎች ለማስተላለፍ ስምምነት ላይ ከደረሱ የኢትዮጵያ ጨዋታዎች በአማራ ቲቪ የሚታይበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ተነግሮናል።