በሴካፋ ውድድር ላይ የሚሳተፉት የኤርትራ እና ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ባህር ዳር ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ከነገ በስትያ የሚጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ እያመሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ባህር ዳር ማምራቱ ሲታወቅ ከትላንት ጀምሮ ደግሞ ከአስተናጋጇ ሀገር ውጪ ያሉ ሀገራት ባህር ዳር እየገቡ ይገኛሉ። የኬንያ ብሔራዊ ቡድንም ትላንት እኩለ ቀን ባህር ዳር መድረሱን ዘግበን የነበረ ሲሆን ምሽት ላይ ደግሞ የኤርትራ እና ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ባህር ዳር መግባታቸው ታውቋል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ባህር ዳር አየር ባረፊያ ሲደርሱም በባህር ዳር ከተማ ከንቲባ፣ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች፣ በስፖርት ቤተሰቦች እና በሚመለከታቸው አካላት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በተለይ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ማረፊያውን ወደሚያደርግበት ኦሊቭ ሆቴል እና ስፖ ሲያመራ ሌላ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል በሆቴሉ እንደተደረገለት ለማወቅ ችለናል።
እስካሁን አራት ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ እና ዩጋንዳ) ባህር ዳር መድረሳቸው ሲታወቅ በዛሬው ዕለት ደግሞ በርካታ ሀገራት ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ሰምተናል።