ሲዳማ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አስፈርሟል

የዝውውር መስኮቱ በይፋ ከተከፈተ አንስቶ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ተጫዋችን ወደ ስብስባቸው መቀላቀል ችለዋል።
በዛሬው ዕለት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው አማካዩ ቴዎድሮስ ታፈሰ ነው። በመከላከያ ባለፉት ዓመታት ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ይህ አማካይ እጅግ ጥቂቶች ብቻ የታደሉትን በመከላከሉ ሆነ በማጥቃት ያለው የላቀ አበርክቶ እንዲሁም አስደናቂ የቆመ ኳስ አጠቃቀም ያለው ሲሆን መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። 

ቡድናቸውን አጠናክረው ለመቅረብ እየታተሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በተለይ በመጀመሪያው ዙር በቀላሉ ግቦች ይቆጠሩበት የነበረው ቡድኑ በቀጣዩቹ ቀናት ሁለት የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ዝውውር ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ቴዎድሮስ ከዝውውሩ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አስተያየት ሰጥቷል።

“ከመከላከያ ስለያይ በጣም ነው ያዘንኩት። ብዙ ነገርን ያየሁበት ቤቴ ነው፡፡ የተለያየሁበትን ምክንያት ወደፊት እገልፃለሁ። አሁን ላይ ግን ምንም መናገርን አልፈልግም። ነገር ግን ስለያይ በጣም ነው ቅር ያለኝ። አሁን ወደ አዲስ ክለብ በመምጣቴ በጣም ደስ ብለኛል። በጣም የምፈልገው ክለብ ነበር፤ ከዚህም ባለፈ ከትልቅ እና ከማከብረው አሰልጣኝ ጋር ለመስራት መምጣቴም የበለጠ ደስታን ፈጥሮኛል።”

ያጋሩ