ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ለሴካፋው ውድድር ተጠርተዋል

ቅዳሜ በሚጀምረው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ አስራ ሰባት ዳኞች ከተለያዩ ሀገራት ጥሪ ሲቀርብላቸው ሁለቱ ከኢትዮጵያ ሆነዋል፡፡

የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ሐምሌ 10 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚደረጉ ሁለት መርሀግብሮች በይፋ ይጀመራል፡፡ በሶስት ምድቦች ተከፍሎ በዘጠኝ ሀገራት መካከል የሚደረገውን ይህን ጨዋታ ከተለያዩ ሀገራት በተመረጡ ዘጠኝ ዋና እና ስምንት ረዳት ዳኞች እንደሚመራ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ለዚህ ውድድር የተመረጠ ሲሆን ከተጋባዣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካባንጋ ማላላ የተባለም ዋና ዳኛ በተጋባዥነት ለዚህ ውድድር ተካቷል፡፡ በዋና ዳኝነት ከብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳም ተመርጠዋል፡፡

በረዳት ዳኝነት ስምንት ዳኞች የተመረጡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኃላሸትን ጨምሮ ከብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ዳኞች ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡

በተያያዘ ከዳኞች ምርጫ በተጨማሪ ሰለሞን ገብረሥላሴ በኮሚሽነርነት፣ ኃይለመላክ ተሰማ እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢው ልዑልሰገድ በጋሻው የውድድሩ ኮኦርድኔተር እና የፊትነስ ኢንስትራክተር በመሆን በሴካፋው ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡