በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪው ሀዋሳ ከተማ ትናንት ወደ ዝውውሩ በመግባት አምስት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ አምስት ፈራሚዎችን ቀላቅሏል፡፡
ግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግሥቱ የዓባይነሽ ኤርቄሎን ቦታ ለመተካት ወደ ክለቡ ተቀላቅላለች፡፡ የቀድሞዋ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ በጌዲኦ ዲላ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት አሳልፋለች።
ቱሪስት ለማ የክለቡ አዲሷ ተጫዋች ነች። የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቿ አርባምንጭ ከተማን ከለቀቀች በኃላ የተጠናቀቀውን የውድድር አመት በጌዲኦ ዲላ ያሳለፈች ሲሆን ባሳየችው የዘንድሮው ድንቅ አቋም መነሻነት ክለቡን በለቀቀችሁ አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ምትክ በከፍተኛ ክፍያ ወደ ሀዋሳ አምርታለች፡፡
እታለም አመኑ ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ ነች፡፡ የተከላካይ አማካይዋ በወላይታ ድቻ ኳስን ከጀመረች በኃላ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ መጫወት የቻለች ሲሆን በድሬዳዋ በመጫወት ካሳለፈች በኋላ በድጋሚ የቀድሞ ቡድኗ ሀዋሳን ዳግም ለማገልገል ፊርማዋን አኑራለች፡፡
የግራ መስመር ተከላካይዋ ፀሀይነሽ በቀለ ወደ የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረን ስብስብ የተቀላቀለች ሌላዋ ተጫዋች ናት፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈችው የመስመር ተከላካይዋ ለተሰላፊነት ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዓመቱን በአቃቂ ቃሊቲ አስደናቂ አቋሟን በማሳየት ያጠናቀቀችው የቀድሞዋ የደደቢት እና ጥረት አማካይ ኪፊያ አብዱራህማን ሌላኛዋ የክለቡ አዲስ ተጫዋች ሆናለች፡፡
ክለቡ በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ ተጫዋቾችን ያስፈርማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡