ኢትዮጵያ ቡና ያልተጠበቀ ዝውውር አጠናቋል

በአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ልምድ ያለውን የመስመር ተከላካይ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ13 ነጥቦች ተበልጦ ዋንጫውን በፋሲል ከነማ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና ክፍተቶቼ ባላቸው ቦታዎች ላይ ዝውውሮችን ማድረግ ጀምሯል። ከሁለት ቀናት በፊት የግብ ዘቡ በረከት አማረን ዝውውር ያጠናቀቀው ክለቡ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋርም ድርድር ላይ መሆኑ ሲታወቅ ከደቂቃዎች በፊት ግን አንጋፋው የመስመር ተከላካይ ሥዩም ተስፋዬን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙ ታውቋል።

የቀድሞ የመተሐራ ስኳር እና ኒያላ ተጫዋች ሥዩም 2003 ላይ ኤሌክትሪክን ለቆ ወደ ደደቢት ካመራ በኋላ የእግርኳስ ህይወቱ ከፍታ ላይ መድረስ ችሎ ነበር። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲያልፍ በስብስቡ ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው። የቀኝ መስመር ተከላካዩ የሊጉ ቻምፒዮን ከሆነበት ደደቢት ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ማምራቱ በዛም የሊጉ አሸናፊ መሆኑ የማይዘነጋ ሲሆን በዘንድሮ የውድድር ዓመት ወደ ወልቂጤ፤ በአጋማሹ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን ተቀላቅሎ ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር።

ኢትዮጵያ ቡናዎችም በስብስባቸው ውስጥ እንዳለ የሚታሰበውን የልምድ ችግር ለመቅረፍ ታስቦ በሚመስል መንገድ የመስመር ተከላካዩን የግላቸው ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።