ከሰዓታት በፊት ሥዩም ተስፋዬን ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ደግሞ የመሐል ተከላካይ በይፋ አስፈርመዋል።
በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣይ የውድድር ዓመት የበለጠ ተጠናክሮ ለመምጣት በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ደህረ-ገፃችን ከዚህ ቀደም እንዳስነበበችው የግብ ዘቡ በረከት አማረ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሥዩም ተስፋዬ ከጅማ አባጅፋር ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርተዋል። አሁን በተገኘ መረጃ ደግሞ ቁመታሙ የመሐል ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ የቡናማዎቹን መለያ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለመልበስ ተስማምቷል።
በኦሮሚያ ምርጥ ውድድር ላይ ባሳየው አቋም ለአርሲ ነገሌ መጫወት የጀመረው ቴዎድሮስ ወደ አዳማ ከተማም አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ከዛም ከአዳማ ወጥቶ ወደ መከላከያ በማቅናት ለአራት ዓመታት በጦሩ ቤት ግልጋሎት ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ዋንጫ ያነሳበትን መከላከያ በመልቀቅ ዳግም ወደ አዳማ አቅንቶ የነበረው ተጫዋቹም ዘንድሮ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ተከትሎ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አቅንቶ ድንቅ የውድድር ዓመት አሳልፏል። አሁን ደግሞ የመዲናውን ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን ለማገልገል ፊርማውን ማኖሩ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።