ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨዋታ በፊት እንደሚደረግ መርሐ-ግብር ተይዞለት የነበረው የዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ ወደ እሁድ ተዘዋውሯል።
ከነገ በስትያ የሚጀምረው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ውድድር በዘጠኝ ሀገራት መካከል ይደረጋል። የውድድሩ የምድብ ድልድል በበይነ-መረብ አማካኝነት ከወጣ በኋላ የጨዋታዎቹ ቀን እና ሰዓታት ይፋ ሆኖ ነበር። በሴካፋ አማካኝነት ይፋ በሆነው መረጃ መሠረት ውድድሩ ቅዳሜ ሲጀምር 8 ሰዓት ላይ ዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ እንደሚጫወቱ ተጠቁሞ ነበር። ይህ መረጃ በብዙዎች ዘንድ የነበረ ቢሆንም የውድድሩ ተጋባዥ ሀገር የሆነችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ ኢትዮጵያ የምትመጣው ነገ (ዓርብ) መሆኑን ተከትሎ የዩጋንዳ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ ወደ እሁድ 7 ሰዓት ዞሯል።
ከዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ በኋላ እንደሚደረግ ቀድሞ የተገለፀው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨዋታ ደግሞ ብቸኛው የቅዳሜ መርሐ-ግብር እንደሆነ ተገልጿል። የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ 9 ሰዓት ከመደረጉ በፊትም ደማቅ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ከ8 ሰዓት ጀምሮ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ነግረውናል።