እስካሁን ሦስት ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
ዋና አሠልጣኝ ከመሾማቸው በፊት በዝውውር ገበያው ላይ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከቀናት በፊት ጋቶች ፓኖምን የግላቸው ማድረጋቸው ይታወሳል። ሶከር ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት በዘገበችው የዝውውር ዜና መሠረትም ትናንት ክለቡ የቸርነት ጉግሳን እና የበረከት ወልዴን ዝውውር አጠናቋል። አሁን ከምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ክለቡ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንደተስማማ ይጠቁማሉ።
ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የመጀመሪያው ተጫዋች ግዙፉ የመሐል ተከላካይ ምኞት ደበበ ነው። የቀድሞ የደደቢት ተጫዋች የነበረው ምኞት ውሀ ሰማያዊ ለባሾቹን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ማምራቱ አይዘነጋም። በአዳማ ቤትም ለአራት ተከታታይ ዓመታት ከተጫወተ በኋላ ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ሀዋሳ ከተማ አቅንቶ ነበር። በሀዋሳም ድንቅ የውድድር ዓመት በማሳለፍ የእግርኳስ ህይወቱን በፈረሰኞቹ ለመቀጠል በዛሬው ዕለት ተስማምቷል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የመሐልም ሆነ የመስመር አጥቂ ሆኖ መጫወት የሚችለው ቡልቻ ሹራ ነው። በ2008 በአዳማ ወጣት ቡድን ባሳየው ድንቅ አቋም ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ቡልቻ ጥሩ ዓመታትን በማሳለፍ ራሱን አጎልብቷል። በዘንድሮው የውድድር ዘመንም ሰበታ ከተማን በመቀላቀል ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር።
የፈረሰኞቹን መለያ በቀጣዩ ዓመት ለመልበስ ስምምነት የፈፀመው ሦስተኛው ተጫዋች ሱሌይማን ሰሚድ ነው። ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የተገኘት ሱሌይማን በአዳማ ከተማ ለሦስት ዓመታት መልካም ቆይታን ካደረገ በኋላ የቀድሞው አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለን ተከትሎ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አምርቶ ነበር፡፡ ከሀዲያ ጋር ያለው ውል መገባደዱን ተከትሎም የመዲናውን ክለብ ተቀላቅሏል።
የሦስቱን ተጫዋቾች ዝውውር ክለቡ ዛሬ አልያም ነገ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።