ዋልያዎቹ በቅዳሜው ጨዋታ አጥቂያቸውን ያጣሉ

ከነገ በስትያ የኤርትራ አቻውን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ተጫዋቹን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ አድርጓል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 4 ጀምሮ ለምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሲዘጋጅ ከርሟል። ብሔራዊ ቡድኑ መቀመጫውን በካፍ የልህቀት ማዕከል በማድረግ ልምምድ ሲሰራ የሰነበተ ሲሆን በመሐልም ከሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሲያደርግ ነበር። በሳምንቱ መጀመሪያ ደግሞ ወድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር በማምራት የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ማድረግ ይዟል።

23 ተጫዋቾችን በመያዝ በብሉ ናይል ሆቴል (አቫንቲ) ማረፊያውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑም ወደ ባህር ዳር ሲጓዝ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረውን መስፍን ታፈሰን በቅዳሜው ጨዋታ እንደማያገኝ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል። መስፍን ከ5 ቀናት በፊት (ከመድኑ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሁለት ቀን በኋላ) በልምምድ ላይ እያለ ባጋጠመው የታፋ ጉዳት ምክንያት ከቡድን አጋሮቹ ጋር የጋራ ልምምድ ሲሰራ አልነበረም። እርግጥ የተጫዋቹ ጉዳት መጠነኛ መሻሻል እንዳሳየ ቢገለፅም ከቅዳሜው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ተጠቁሟል። ምናልባት ግን በሁለተኛው የቡሩንዲ የምድብ ጨዋታ ሊደርስ እንደሚችል ተነግሯል።