በሴካፋ ውድድር ላይ የሚካፈለውን የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በአምበልነት የሚመሩት ተጫዋቾች ዝርዝር ታውቋል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ በሚጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ከሰኔ 4 ጀምሮ ልምምዱን በአዲስ አበባ ከዛም በባህር ዳር ሲያከናውን ቆይቷል። 23 ተጫዋቾችን የያዘው ቡድኑም ነገ ከኤርትራ አቻው ጋር ከመጫወቱ በፊት ዛሬ ከሰዓት የመጨረሻ ልምምዱን እንደሚሰራ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት የሚመሩት ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ ታውቋል። በዚህም የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ አቡበከር ናስር የብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ አምበል እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ከአቡበከር በመቀጠል ደግሞ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ሀብታሙ ተከስተ የቡድኑ ሁለተኛ አምበል መሆኑ ተነግሮናል።