ሀድያ ሆሳዕና የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፀመ

በፌዴሬሽኑ በቅርቡ ዕግድ የተጣለበት ሀዱያ ሆሳዕና ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ፡፡

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን በቅርቡ በሁለት አመት ውል የቀጠረው ሀድያ ሆሳዕና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከተጫዋቾቹ ጋር በገባው እሰጣ ገባ መነሻነት ፌድሬሽኑ በክለቡ ላይ የዕግድ ውሳኔ ማሳለፍ ይታወሳል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የክለቡ የበላይ አካላት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ጋር ባደረጉት ንግግር ይህን ችግር ለመፍታት በዚህ ሳምንት ቀጠሮ የያዙ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ግን ክለቡ ተጠናክሬ መቅረብ አለብኝ በሚል በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ ጎራ በማለት ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በሁለት ዓመት ውል በይፋ ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

የመጀመሪያው ፈራሚ አጥቂው ስንታየው መንግሥቱ ሆኗል፡፡ ከወላይታ ድቻ ታዳጊ ቡድን 2007 ላይ ካደገ በኃላ እስከ 2010 ድረስ በዋናው ቡድን በመጫወት የጀመረ ሲሆን ከቡድኑ ከተለያየም በኃላ በሀላባ ከተማ፣ አርባ ምንጭ ከተማ እና እና በ2012 የውድድር ዘመን ደግሞ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሶ በባህር ዳር ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወደ ቀደሞ ክለቡ ወላይታ ድቻ ከተመለሰ በኃላ እጅግ አስገራሚ ብቃቱን በማሳየቱ በበርካታ ክለቦች መፈለግ ቢችልም በመጨረሻም ማረፊያው የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ሀድያ ሆሳዕና ሆኗል፡፡

እንደ ስንታየው ሁሉ ወላይታ ድቻን በመልቀቅ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ያመራው ፀጋዬ ብርሀኑ ነው፡፡ በ2008 ከወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኃላ ለስድስት አመታት በወጥነት ክለቡን ያገለገለው ይህ የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊ ዘንድሮ በጦና ንቦቹ ቤት በተለይ ተቀይሮ ሲገባ ግብ ሲያስቆጥር የምናየው ሲሆን ለከርሞ የነብሮቹ አዲሱ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ሦስተኛው የክለቡ ፈራሚ ብርሀኑ በቀለ ነው፡፡ የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ የመስመር አጥቂ እና ተከላካይ ቢጫ ለባሾቹን በ2012 መስከረም ወር ላይ ከለቀቀ በኃላ በሀዋሳ ከተማ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታትን ማሳለፍ ችሏል፡፡ ለቀጣዩቹ ሁለት አመታት ደግሞ በሀድያ ሆሳዕና መለያ ለመታየት የቀድሞው አሰልጣኙ ሙሉጌታን እግር ተከትሎ አቅንቷል፡፡