ቅዱስ ጊዮርጊስ የአራት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

ወደ ዝውውር ገበያው በይፋ በመግባት ሦስት አዳዲስ እና አንድ ነባር ተጫዋችን አስፈርሞ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን የአራት ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት ማራዘሙ ታውቋል።

የምንጊዜም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከለመደው የዋንጫ ስኬት እየራቀ መጥቷል፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የፈፀመው ክለቡ ወደ ለመደው የዋንጫ ተፎካካሪነት ለመመለስ ራሱን ለማጠናከር የቤት ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ለቀጣዩ የ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ ጋቶች ፓኖም፣ ቸርነት ጉግሳ እና በረከት ወልዴ ወደ ክለቡ በአዲስ መልክ ያመጣ ሲሆን የተከላካዩ ሳልሃዲን በርጌቾንም ውል በቅርቡ ማደሱ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕለት ደግሞ የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌይሬሽን ፅህፈት ቤት ለሁለት ተጨማሪ አመት እንዲራዘምላቸው አድርጓል፡፡

አማካዩ ሀይደር ሸረፋን ለሁለት ተጨማሪ ዓመት በክለቡ መቆየቱ ዕርግጥ ሆኗል ፡፡የቀድሞው የደደቢት፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባቡና እና መቐለ 70 እንደርታ አማካይ 2012 ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ካመራ በኋላ ሁለት የውድድር ዓመታትን በክለቡ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ውሉ በያዝነው ወር መጀመሪያ መጠናቀቁን ተከትሎ ተጫዋቹ ለተጨማሪ ሁለት አመት መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው ናትናኤል ዘለቀ ነው፡፡ ቁመተ መለሎው የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ከፈረሰኞቹ የታዳጊ ቡድን ካደገ በኋላ በወጥነት ለስድስት ተከታታይ ዓመት በዋና ቡድን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በተወሰነ መልኩ ጉዳት ገጥሞት በበቂ መልኩ ክለቡን ማገልገል ባይችልም በዛሬው ዕለት ግን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በይፋ በፌድሬሽኑ ፊት ቀርቦ ውሉን አድሷል፡፡

ውሉን ያራዘመው ሌላኛው ተጫዋች አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል ነው፡፡ በመስመር እና በፊት አጥቂነት የሚጫወተው የቀድሞው የዳሽን ቢራ እና የመቐለ 70 እንደርታ ተጫዋች ከመቐለ ጋር የአንድ ቀሪ ዓመት እየቀረው በአካባቢው በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ፌዴሬሽኑ ባዘዘው መመሪያ መሠረት ወደ ፈረሰኞቹ ቤት አምርቶ የአንድ አመት ቆይታን ያደረገ ሲሆን ምናልባት መቐለ በሊጉ ከቀጠለ ውል ስላለበት ወደ ክለቡ ያመራል ተብሎ ቢጠበቅም በዛሬው ዕለት ግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፅህፈት ቤት ተገኝቶ ለሁለት ተጨማሪ ዓመት በቅዱስ ጊዮርጊስ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡

ደስታ ደሙ አራተኛው ውል ያደሰ ተጫዋች ነው። የቀድሞ የሙገር፣ ደደቢት እና ወልዋሎ ተከላካይ ዘንድሮ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ከተለያዩ አጣማሪዎች ጋር በመጫወት ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

ረፋድ ላይ ከምኞት ደበበ፣ ቡልቻ ሹራ እና ሱለይማን ሰሚድ ጋር ክለቡ እንደተስማማ የገለፅን ሲሆን ሦስቱን ተጫዋቾችም ፌድሬሽን በመገኘት የሁለት ዓመት ውልን ከክለቡ ጋር መፈራረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡