ትንሽ ክለብ ትልቅ ልብ – ኮልፌ ቀራንዮ

አጭር ዕድሜ፤ የተለየ የጨዋታ መንገድ፤ ፈጣን ዕድገት… ይህ ሁሉ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለአንድ ተጫዋች ዝውውር ከሚያወጡት ገንዘብ ባነሰ ዓመታዊ በጀት ብዙዎችን አስደምሞ የፕሪምየር ሊግን በር አንኳክቶ የተመለሰው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ እግርኳስ ክለብ መለያ ነው። በዚህ ፅሁፍም የክለቡን ጉዞ እና ከዚህ ግስጋሴ ጀርባ ስላለው ቁልፍ ሰው ሀሳቦችን ለማንሳት ወደናል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በመንግስት የልማት ድርጅቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደገፉ የእግርኳስ ቡድኖች ቁጥር እጅግ እየተመናመነ በምትካቸው በርከት ያሉ የከተማ አስተዳደር ቡድኖች በሀገሪቱ የፉክክር እግርኳስ መድረኮች ላይ እየተመለከተን እንገኛለን። የእነዚህ ክለቦች መበራከት በተለይ በእግርኳሱ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን ከቀደሙት ዘመናት አንፃር የላቀ እንዲሆን እና በተወሰኑ ከተማዎች ብቻ ተወስኖ የነበረው የሀገራችን እግርኳስ በመላው ሀገሪቱ በሚባል መልኩ እንዲሰራጭ ብሎም በስፖርቱ ዙርያ ላሉ አካላትም ሰፊ እድልን መፍጠራቸው በጥሩነት ቢወሳም በተወሰነ መልኩም አካሄዳቸውን ሆነ እግርኳሳዊ ባልሆኑ መንገዶች ስማቸው በመጥፎ መነሳቱ አልቀረም።

ለአብነትም መዲናችን አዲስ አበባ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሀገሪቱ ሁለተኛ የውድድር እርከን በሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገውን አዲስአበባ ከተማን ጨምሮ በመዲናይቱ አስተዳደር በቀጥታ የሚደገፉ አራት የክፍለከተማ ቡድኖች አሳትፋለች። የክፍለከተማዊ ቡድኖች በመሰረታዊነት በትልቅ ደረጃ የሚፉካከሩ ቡድኖችን መያዛቸው ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን ክርክር ወደ ጎን ትተን በከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ከነበሩት ቡድኖች ግን ኮልፌ ቀራንዮ የተሻለውን ጊዜ ማሳለፍ የቻለው ቡድን ነበር።

በ2010 ዓ.ም እንደ አዲስ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ባለቤትነት የተቋቋመው ክለቡ በመጀመሪያ ዓመቱ አዲስ አበባን በመወከል በክልል ክለቦች ሻምፒዮና የተሻለ ውጤትን በማስመዝገብ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የተሸጋገረ ሲሆን በቀጣዩ የውድድር ዘመንም ከኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ባቱ ከተማን ተከትሎ በሁለተኝነት ደረጃ በማጠናቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሲቀላቀል በ2013 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ “ሐ” ከአርባ ምንጭ ከተማ በጥቂት ነጥቦች ርቆ በሁለተኝነት በማጠናቀቁ የትግራይ ክልል ክለቦች በቀጣዩ የውድድር ዘመን የማይካፈሉ ከሆነ እነሱን ለመተካት በተደረገው የዙር ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ ሆነው ለጥቂት ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቢቀሩም እንደቡድን ፍፁም የተለየ ጊዜን ያሳለፉት እና በአነስተኛ በጀት በተለየ የጨዋታ መንገድ ብዙዎች ማስገረም ችለዋል።

ስለአስደናቂው የውድድር ዘመናቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ያደረገው አሰልጣኝ መሀመድ ኑር በአነስተኛ በጀት ስኬታማ ቡብን ስለገነባበት ምስጢር ይናገራል።

“በቅድሚያ የተነሳነው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መፍትሄ የሚሆን የጨዋታ መንገድ እንዳለ ለማሳየት ነው ፤ ይዘንውም የመጣነው መንገድ ወጣት ተጫዋቾችን መሰረት ያደረገ እና ተጫዋቾች አቅማቸውን በነፃነት እንዲያወጡ የሚያስችል የስልጠና መንገድን በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችለናል። እኔ በግሌ እግርኳስን የምረዳው እና የምገነባቸው ቡድኖች መገለጫ እንዲሆን የምፈልገው ኳስን ከራሱ የግብ ክልል ጀምሮ መስርቶ የሚጫወት ኳስን እንደልቡ ተቆጣጥሮ የሚያጠቃ ቡድን ነው። ይህንንም በኮልፌ ለማድረግ ሞክረናል። እርግጥ ይህ አጨዋወት ጊዜ የሚፈልግ እንደመሆኑ የክለቡ አመራሮች እየሰራነው ባለው ነገር አምነው በነፃነት እንድንሰራ ስለፈቀዱልን ማመስገን እፈልጋለሁ። ቡድኑን ከማዋቀር ሒደት አንስቶ የተለየ መንገድን ለመከተል ሞክረናል እኔ በግሌ እግርኳስን በተመልካችነትም ሆነ በስልጠናው ረዘም ያለ ጊዜያትን ያሳለፉት ከታዳጊዎች ጋር መሆኑ ይበልጥ ጠቅሞኛል። እኛ መከተል ለምንፈልገው የጨዋታ መንገድ የሚሆኑ እና በሌሎች ክለቦች በተለያዩ ምክንያቶች የመሰለፍ እድል ያጡ ወጣት ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ተግባብተን እና በተቀናጀ መንገድ ፍፁም ዲሲፕሊን በተሞላበት መንገድ እጅግ አነስተኛ በሆነ በጀት የተሻለ ነገር ለማሳካት ጥረት አድርገናል።”

በእግርኳሳችን እንደ ከፍተኛ ማነቆ ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል የአማራጭ ሀሳቦች ጉዳይ አንዱ እና ዋነኛው ነጥብ ነው። ለአብነትም በውድድሮች የሚካፈሉ ሁሉም ቡድኖች ማለት በሚቻል ረገድ ውጤታማ ቡድኖችን የመገንቢያው ቁልፍ ተደርጎ የሚወሰደው ጉዳይ ከፍ ያለ በጀትን በመመደብ በውድድሩ አውድ ልምድ ያካበቱ አሰልጣኞችን መቅጠር በየዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የማዘዋወር ዝንባሌ የተለመደው የእግርኳሳችን የአሰራር መንገድ እንደሆነ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።

ታድያ በፕሪምየር ሊጉም ሆነ በከፍተኛ ሊግ በተነፃፃሪነት በክለቦቹ የሚያዘው በጀት በተወሰነ መልኩ ልዮነት ቢኖረውም ሁሉም ቡድኖች በሚባል መልኩ ይህን የተለመደ መንገድ ለመከተል ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል። እርግጥ በዚህ መንገድ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ቡድኖችን መጥቀስ ቢቻልም በዚሁ አካሄድ ተጉዘው ውጤታማ መሆን የተሳናቸውን ቡድኖችን እንዲሁ መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህም መነሻነት ቡድኖች አማራጭ መንገዶችን ለመከተል ተነሳሽነቱን ሆነ ድፍረቱን ሲያሳዩ እምብዛም አንመለከትም። በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለይ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የተመለከትናቸው የደደቢት እና የአዳማ ከተማ ምንም እንኳን በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የተደረጉ የአካሄድ ለውጦች ቢሆኑም ከቀደመው መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች የተለየ መንገድ ለመጓዝ ሞክረው ውጤታማ መሆን አለመቻላቸው በተወሰነ መልኩ ክለቦች ከተለመደው መንገድ መውጣትን በአውንታዊ መልኩ እንዲመለከቱት ሊያስገድዱ ይችላል።

አሰልጣኝ መሐመድ ኑር በእግርኳሳችን ውስጥ ልምድ ላላቸው ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ስለሚሰጠው የተለየ ትኩረት ተከታዩን ሀሳቡን ሰጥቶናል።

“በግሌ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ሆነ አሰልጣኝ አያስፈልግም ባልልም ወጣቶች ላይ መሰረት ያደረገ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ ፤ እርግጥ በተወሰኑ የሜዳ ክፍሎች(ግብጠባቂ ፣የመሀል ተከላካይ….) ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩ በጣም ይጠቅማል ነገርግን ልምድ ባላቸው ብቻ የሚለው አካሄድ ብዙም አያስኬድም። በእኛ ቡድን ከሌሎች ቡድኖች ባነሰ በጀት እንደመንቀሳቀሳችን ለምንፈልገው የጨዋታ መንገድ የሚሆኑ ከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ይዘን ለመጓዝ ጥረት አድርገናል። በተመሳሳይ በክለቦች የምንመለከተው የውጭ ተጫዋቾችን መሰብሰብ እንዲሁ በፍፁም መሆን የሌለበት ነው ፤ ቡድኖች በኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች እነሱን ባማከለ ስልጠና መገንባት አለባቸው ብዬ አምናለሁ ይህን ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ተመልክተናል ቡድኖች ተጫዋቾች ባለቸው ነገር ላይ መስራት ከቻሉ ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያየነው ስለሆነ በቀጣይ ይበልጥ በዚህ ዙርያ መስራት ይገባናል።”

በዚህ ፅሁፍ ለማንሳት የወደድነው ክለብ ግን ይህን አካሄድ የሰበረ በቀጣይም ለሌሎች ክለቦች ምሳሌ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተለየ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገንዘብ እና ውጤታማነትን ለመነጣጠል እስኪከብድ ድረስ በክለቦች የእግርኳስ ውድድሮች ላይ ውጤታማ እየሆኑ ከሚገኙ ክለቦች በስተጀርባ የፈረጠመ የፋይናንስ አቅርቦት መኖሩ እርግጥ ነው። በዚህ ሒደት ታድያ መሰል የገንዘብ አቅም የሌላቸው ቡድኖች ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል “ከሀብታሞቹ” ክለቦች በተለየ መንገድ መጓዝ የግድ ይላቸዋል።

በኮልፌ ቀራንዮም የሆነው ይህ ነው 20 ሚልየን የተሻገረ ዓመታዊ በጀትን የሚይዙ ቡድኖች በበዙበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከአራት ሚልየን ብር ባነሰ አመታዊ በጀት የሚዘወረው ቡድን ብዙዎችን ባስደመመ መንገድ ድንቅ የውድድር ዘመን ማሳለፍ ችሏል።

በአነስተኛ በጀት መወዳደር በቅድሚያ ከሚደቅናቸው ስጋቶች አንዱ አሰልጣኞች መከተል ለሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ የሚስማሙ በንፅፅር የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾች ማዘዋወር እንዳይችሉ ማድረጉ ነው። ኮልፌዎችም ይህን ተግዳሮት እንደ እድል ተጠቅመውበታል በሚያስብል መልኩ በድንቅ ምልመላ ከዚህ ቀደም ተጠቃሽ የቀደመ ይህ ነው የሚባል ታሪክ የሌላቸውን እና ከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ያላቸውን ወጣት ተጫዋቾች በማሰባሰብ ይህን አስደናቂ ታሪክ መፃፍ ችለዋል።

ከዚህ ውጤታማ ምልመላ ጀርባ ቁልፉ ሰው ወጣቱ አሰልጣኝ መሀመድኑር ንማ ይሰኛል። በተጫዋችነት ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ ታሪክ የሌለው ወጣቱ አሰልጣኝ ወደ በትልቅ ደረጃ ቡድኖችን ማሰልጠን ከመጀመሩ አስቀድሞ ታዳጊ ወጣቶች ላይ በሰራቸው አስደናቂ ሥራዎች የበርካቶችን ቀልብ መግዛት ችሏል።

አሰልጣኙም አሁን በፕሪምየር ሊግ እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል እንደነ ሰልሀዲን በርጌቾ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ቶማስ ስምረቱ አቡበከር ሳኒ፣ እሱባለው ሙሉጌታ እና ሬድዋን ናስርን የመሰሉ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው አሰልጣኙ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወንድም በሆነው እንዳለእየሱስ አባተ አማካኝነት በ2009 የውድድር ዘመን የአዲስአበባ ከተማን ከ17 አመት በታች ቡድንን በማሰልጠን በከፍተኛ ደረጃ ማሰልጠን “ሀ” ብሎ የጀመረው አሰልጣኙ ቡድኑን የውድድሩ አሸናፊ በማድረግ የአሰልጣኝነት ጉዞውን ጀምሯል።

በመቀጠልም ከ2010 አንስቶ በወቅቱ የአዲስአበባ አንደኛ ዲቪዝዮን ተካፋይ የነበረውን ኮልፌ ቀራንዮን ተረክቦ ቡድኑን በዚያኑ አመት ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ እንዲቀላቀል አስችሏል ፤ በቀጣዩ የውድድር ዘመንም ቡድኑ ከኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሲሸጋገር አምናም በተሰረዘው የውድድር ዘመን በመጀመሪያው ዙር አስቸጋሪ ጊዜያትን ቢያሳልፉም በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ የተሻለ ጊዜን ማሳለፍ በጀመሩበት ወቅት የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ውድድሩ ሊሰረዝ በቅቷል።

ዘንድሮም በአሰልጣኝ መሀመድኑር ንማ የሚመራው ቡድኑ ከፍተኛ ጉልበት ፣ ፍጥነት እና ቀጥተኝነት መገለጫው በሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ፍፁም በተለየ መንገድ የኳስ ቁጥጥርን መገለጫው የሆነን አስደማሚ ቡድን ገንብተው ለብዙዎች ትምህርትን መስጠት ችለዋል ፤ እርግጥ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እንደሌሎች እግርኳሳዊ ውድድሮች በተመረጡ ከተሞች መደረጉ እና ያለተመልካች መደረጉ የሰጣቸው ጥቅም እንዳለ ሆኖ አስቸጋሪ መልክ በተላበሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን በዚህ መልኩ በመቅረብ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በማሳየታቸው ግን አድናቆት ይገባቸዋል።

እርግጥ የእግርኳስ ቡድኖች ስኬት የሚለካው ባሳኩት ዋንጫ አልያም ባሳኩት ግብ ቢሆንም ከመጨረሻው ውጤት ባለፈ በሂደቱ ስኬትን መለካት ግን አንዳንዴ የግድ ይላል። በኮልፌ ቀራንዮ በኩል የሆነውም ይህ ነው ቡድኑ የውድድር ዘመኑን በጀመረበት አስደናቂ መንገድ ውድድሩን ማጠናቀቅ ባይችልም በእራሳቸው መንገድ ለዚህ መብቃታቸው በራሱ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ እግርኳስ ከሚነሱ አስደናቂ ታሪኮች አንዱን አፅፈው ማለፍ ችለዋል።

በመጨረሻም አሰልጣኝ መሐመድኑር ውጤታማ እንዲሆን ለረዱት አካላት ምስጋናውን እንዲህ ሲል አቅርቧል።

“በቅድሚያ እዚህ ለመድረሳችን ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። በማስቀጠል አብረውኝ ይሰሩ የነበሩት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት መላው የቡድኑ አባላት በተለይም አምበላችንን ፈቱ አብደላ አመሰግናለሁ።በመጨረሻም ለእኔ በስልጠናው እዚህ እንድደርስ ያገዙኝን ቤተሰቦችን በተለይ ታላቅ ወንድሜ እስማኤል ገና ከጅምሩ በብዙ ነገር ያግዘኝ ነበር በመጨረሻም በትልቅ ደረጃ እንዳሰለጥን እድሉን ላመቻቸልኝ እንዳለየሱስ አባተ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።”

እርግጥ በተለያየ ምክንያት ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የነበረው ተስፋ እውን መሆን ባይችልም በክለቡ ዙርያ የነበሩት አካላት በሙሉ ከዚህ አስደናቂ ጉዞ በስተጀርባ ለነበራቸው አበርክቶ የተለየ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ታድያ ለቡድኑ ከባድ ፈተና የሚሆነው ይህን ሂደት በቀጣይ ዓመት እንዴት ማስቀጥል ይችላሉ የሚለው ነው ከወዲሁ በቡድኑ ጥሩ ጊዜያትን ያሳለፉ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን በሌሎች ክለቦች እየተነጠቁ የሚገኙት አሰልጣኙ በቀጣይ ይህን ስብስብ ዳግም ጠግነው በምን መልኩ ይቀርባሉ የሚለው ጉዳይ ከወዲሁ ይጠበቃል። ሌሎችም ቡድኖች ከዚህ የኮልፌ ቀራንዮ ተሞክሮ ልምድ በመውሰድ በቀጣይ እንደነባራዊ ሁኔታቸው መሰረት ያደረገ እና ውጤታማ ሊያደርጋቸው የሚችልን መንገድ በመቀየስ ብዝሃ ሀሳቦች እና የተሻለ ፉክክር የሚታይበት እግርኳስ ለመፍጠር መታተር ይኖርባቸዋል።