ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ አሁንም ተጫዋች ማስፈረሙን ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊው ሀዋሳ ከተማ የአዳዲስ ፈራሚዎችን ቁጥር ወደ አስራ ሁለት ያደረሰ ሲሆን የሁለት ታዳጊዎችን ውልም አራዝሟል፡፡

ሕይወት ረጉ (ካኑ) በይፋ በሁለት ዓመት ሀዋሳን የተቀላቀለች አዲሷ ተጫዋች ነች፡፡ የቀድሞዋ የአለቤ ሾው እና ደደቢት ድንቋ አማካይ ያለፉትን ዓመታት በመከላከያ ድንቅ ብቃቷን ስታሳይ የነበረች ሲሆን ከ2004 ጀምሮም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም ተጫውታ አሳልፋለች፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መከላከያ ሁለተኛ ሆኖ ሲፈፅም ትልቁን ድርሻ የተወጣችሁ የመሐል ሜዳ አማካይዋ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በሀዋሳ መለያ የምንመለከታት ይሆናል፡፡

ሌላኛዋ ፈራሚ ምኅረት ተሰማ ነች፡፡ በግራ እና ቀኝ የመስመር ተከላካይነት በሀዋሳ ከተማ የእግር ኳስ ህይወቷን የጀመረችው ተጫዋቿ ሀዋሳን በመልቀቅ ወደ መከላከያ አምርታ ስድስት ዓመታት በወጥነት ቡድኑን ካገለገለች በኃላ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቧ ተመልሳ የሁለት ዓመት ውል አስፍራለች፡፡

በተጨማሪም ክለቡ ከታዳጊ ቡድን አሳድጓቸው የነበሩት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ህይወት ቶማስ እና እሙሽ ዳንኤልን ውልም ለሁለት ዓመት ማራዘሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡