የሴካፋ መክፈቻ ጨዋታ ስድስት ግቦችን ተስተናግዶበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ያገናኘው የሴካፋ የመጀመሪያ ጨዋታ ከማራኪ እንቅስቃሴ ጋር 3-3 ተጠናቋል።

በጨዋታው ጅማሮ የኤርትራ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ የቻለ ሲሆን በ2ኛ ደቂቃ በተከታታይ ስህተት የተገኘውን ኳስ የኤርትራው የመስመር አጥቂ ደህያን ግብሳዊን ወደ ግብ ሞክሮ ግብጠባቂ አድኖበታል። በድጋሚ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከቀኝ መስመር ከዓሊ የተሻገረለትን ኳስ ደህያን በድጋሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከደቂቃዎች በኋላ ዓሊ ሱሌይማን  በግራና በቀኝ መስመር ከሚፈጥረው ያሻማውን ኳስ ሳዶር ደያስ ሳይደርስበት ቀርቷል። 

ተረጋግተው በመጫወት ቀስ በቀስ ጨዋታውን መቆጣጠር የጀመሩት ዋልያዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከ አቡበከር ከተሰጠው ኳስ በግራ ሳጥን ጠርዝ ባደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ወደ ጎል ተጠግተዋል። 12ኛ ደቂቃ ላይ ደግመሞ ዊሊያም ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኢትዮጵያን ቀዳሚ አድርጓል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂ ያዳነበትም የኢትዮጵያን መሪነት ማስፋት የምትችል ነበረች።

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የጎል ሙከራዎች ያደረጉት ኤርትራዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ከ ዓሊ የተሰጠውን ኳስ ደህያን ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ በቀረ ኳስ የኢትዮጵያን የኋላ ክፍል ሲፈትሹ 34ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱሌይማን በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረውም ሌላው አጋጣሚ ነበር። 38ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጥረታቸው በተከላካዮች ስህተት ፍሬ አፍርቶ በግል ጥረቱ አሊ ሱሌማን ወደ ግብ ቀይሮ አቻ ሆነዋል።

ጨዋታው በሙከራዎች እና ጎሎች ታጅቦ በመዝለቅ ኢትዮጵያ በድጋሚ መሪ ሆናለች። 43ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር መትቶ የመጀመሪያውን ወደ ውጪ ቢሰደውም ከመመታቱ በፊት ግብ ጠባቂ ከመስመር በመውጣቱ በድጋሚ ረዳት ዳኛው አስደግመው ሁለተኛውን አስቆጥሯል። ሆኖም የኢትዮጵያ መሪነት ከቅፅበት ሳይዘል 44ኛው ደቂቃ ላይ ወዲያው የተጀመረውን ኳስ በኢትዮጵያ ተጫዋቾች ትኩረት ማጣት ዓሊ ሱሌይማን ኤርትራን አቻ አድርጎ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያዊያኑ በተሻለ አቀራረብ እና የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከቸርነት ጉግሳ የተሻገረለትን ኳስ ግብ ጠባቂ  ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ ከዳነበት ከአስር ደቂቃዎች በኋላ 58ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር በግራ ጠርዝ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮ ኢትዮጵያ ዳግም መምራት ችላ ነበር።

በኤርትራ በኩል በተጋጣሚያቸው ብልጫ ቢወሰድባቸውም እንደመጀመሪያው ሁሉ ከዕረፍት መልስም ከአስፈሪ የመልሶ ማጥቃት ኳሶች ግቦችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን 49ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱሌይማን በመልሶ ማጥቃት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ፅዮን አድኖበታል። 51ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ ዓሊ ወደግብ የመታው ኳስ የቀኝ ቋሚ ተጠግቶ ሊወጣበት ችሏል። 

71ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ የገባው ሮሜል አብዱ ላይ ረመዳን ናስር በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዓሊ ሱሌይማን ወደግብ ቀይሮ ለቡድኑ እንዲሁም ለራሱ 3ኛ ግብ በማስቆጠር ሐት ትሪክ ሰርቶ ኤርትራን ከመሸነፍ አድኗታል። ዓሊ ሱሌይማን የመክፈቻው ጨዋታው ኮኮብ ተጫዋች ተብሏል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር በ1980 ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫ ስታነሳ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ለነበሩት ነጋሽ ተክሊት እና አማኑኤል እያሱ ምስላቸው ያረፈበት ስጦታ አበርክተዋል።