በግብፁ ክለብ አል አህሊ እና በደቡብ አፍሪካው ክለብ ካይዘር ቺፍስ መካከል የተደረገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በአህሊ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከ42 የአህጉሪቱ ሀገራት የተወጣጡ 54 ክለቦችን ከመጀመሪያው የቅድመ ማጣሪያ ዙር ጀምሮ ሲያወዳድር የነበረው የ2020/21 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በትናንትናው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል። በፍፃሜው ጨዋታ የተገናኙት የግብፁ አል አህሊ እና የደቡብ አፍሪካው ካይዘር ቺፍስ ጥሩ ፉክክር አድርገው የዘንድሮውን የአህጉሪቱን ትልቁ የክለቦች ውድድር ዘግተዋል።
ምሽት ላይ በተከናወነው ጨዋታ እጅግ ተሽለው የታዩት አህሊዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሦስት ጎሎች ዋንጫውን የግላቸው አድርገዋል። የቡድኑንም ጎሎች መሐመድ ሸሪፍ በ53ኛው ደቂቃ፣ መሐመድ ማግዲ በ63ኛው ደቂቃ እንዲሁም አምሮ ኤልሱልያ በ74ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፈዋል። ድሉንም ተከትሎ አህሊ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለአስረኛ ጊዜ ከፍ ያደረገ ብቸኛው ክለብ ሆኗል።
በጨዋታው ሁለተኛውን ጎል ያስቆጠረው መሐመድ ማግዲ በሁለት ተከታታይ የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ ኮከብ ሆኖ በመመረጥ ታሪክ ሰርቷል። የክለቡ አሠልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ በበኩላቸው ሦስት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያነሱ ብቸኛው አፍሪካዊ አሠልጣኝ ሆነዋል። በአጠቃላይ አህሊ ለሦስተኛ ጊዜ ተከታታይ (2005 እና 2006፣ 2012 እና 2013 እንዲሁም 2020 እና 2021) የመድረኩን ዋንጫዎች አንስቷል።
በትናንትናው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ በተቆጠሩት ሦስት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበረው መሐመድ ሸሪፍ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (በ6 ጎሎች) ሆኖ አጠናቋል።