ያለ አሠልጣኝ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሰርቢያዊ አሠልጣኝ መሾማቸውን አስታውቀዋል።
ክለቡ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የ64 ዓመቱ ስርቢያዊ ዝላትኮ ክራምፖቲች አዲሱ የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ሆነው መሾማቸው ተገልጿል። አስልጣኙ የሰርቢያን ከ17 ዓመት በታች እና ከ19 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ በአፍሪካ የተለያዩ ቡድኖችን በማስልጠን የካበተ ልምድ ያላቸው መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል።
የቀድሞ የሬድ ስታር ቤልግሬድ ተጫዋች ዝላትኮ ክራምፖቲች ከሃያ አምስት ዓመት በላይ በቆዩበት የአሰልጣኝነት ህይወት የደቡብ አፍሪካው ፖልክዋኔ ሲቲ የሩዋንዳው ኤፒአር፣ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ፣ የሰርቢያ ከ19 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና የቲፒ ማዜምቤ (ምክትል) ዋና ዋና የሰሩባቸው ቦታዎች ናቸው። የተሾሙት አሠልጣኝም በቅርብ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች በቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰርዮቪች ሚሉቲች፣ ዱሳን ኮንዲች እና ዝቪጅኖቭ በኋላ የተሾሙ አራተኛ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ሆነዋል።