በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ የገባው ሀዋሳ ከተማ የሦስት ወጣት ተጫዋቾቹን ውል አድሷል።
ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጊምቦ ውላቸውን ካደሱት መካከል ነው፡፡ በሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ተጫውቶ ካሳለፈ በኃላ 2010 ወደ ዋናው ቡድን ያደገው የ2009 ከ20 ዓመት ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂው በኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በተጠናቀቀው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወት የቻለው ግብ ጠባቂው በዋናው ቡድን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ውሉን አራዝሟል፡፡
ሌላኛው ውሉን ያደሰው ወጣት ተጫዋች ፀጋአብ ዮሐንስ ነው፡፡ በ2011 ከሀዋሳ የተስፋ ቡድን ያደገው እና በክለቡ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድሎችን ሲያገኝ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ይህ የመሐል ተከላካይ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በሴካፋ ዋንጫ ተመርጦ ከዓመት በፊት መጫወት የቻለ ሲሆን በሀዋሳ ዋናው ቡድን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ስር ለመሰልጠን ፊርማውን አኑሯል፡፡
ሦስተኛው ወጣት ተጫዋች እና ውሉን ያደሰው አጥቂው ተባረክ ኢፋሞ ነው፡፡ እንደ ፀጋአብ ሁሉ 2011 ላይ ከተስፋ ቡድኑ ወደ ዋናው ያደገው ፈጣኑ የመስመር እና የፊት አጥቂ በክለቡ የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት ለመቀጠል ፊርማውን አኑሯል፡፡
አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን ወደ ማስፈረሙ የገባው ሀዋሳ ከተማ ከሰዓታት በፊት ፀጋሰው ድማሙን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን ተጨማሪ አዳዲስ ፈራሚዎችን ከሰሞኑ ወደ ክለቡ ይቀላቅላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡