ድሬዳዋ ከተማ የአማካዩን ውል አድሷል

በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ዕለት የአማካዩን ውል አድሷል።

የአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ውል በማደስ ለ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ የዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከደቂቃዎች በፊት የአማካዩን ዳንኤል ኃይሉን ውል አድሷል።

የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ ተጫዋች የነበረው ዳንኤል የተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ጅማሮ ላይ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለውን ክለብ (ባህር ዳር ከተማን) ለቆ ወደ ሰበታ ከተማ ማቅናቱ ይታወሳል። በውድድሩ አጋማሽ ላይ ደግሞ በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ተፈልጎ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አቅንቶ ግልጋሎት ሰጥቷል። የተጫዋቹ ውል መጠናቀቁን ተከትሎም የክለቡ አመራሮች ተጫዋቹ እንዲቀጥል ውይይት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን ድርድሩ ፍሬያማ ሆኗል። በዚህም ተጫዋቹ የሁለት ዓመት ውል በፌዴሬሽን ተገኝቶ መፈረሙ ታውቋል።

ያጋሩ