በአዳማ ከተማ ለረዥም ዓመታት የተጫወተው ይታገሱ እንዳለ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት ለማገልገል ከስምምነት ደርሷል፡፡
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለት አሰልጣኞችን የለዋወጠው አዳማ ከተማ ከፕሪምየር ሊጉ ቢወርድም በድጋሚ ባገኘው የማሟያ ጨዋታ ራሱን በደንብ በማሻሻል ጥሩ ውጤትን አስመዝግቦ በድጋሚ በሊጉ ላይ መቆየቱን በቅርቡ ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ ለቀጣዩ የውድድር ዘመንም አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን መቅጠሩም ይታወቃል፡፡
የዋና አሰልጣኙን ቅጥር ካገባደደ በኃላ የክለቡን ባህል እና የጨዋታ መንገድ ይረዳል ያሉትን ረዳት አሰልጣኝ ለመቅጠር የክለቡ ቦርድ ካጤነ በኃላ በክለቡ በተለያዩ ወቅቶች በድምሩ 11 ዓመታትን በአማካይነት እና በአምበልነት የመራው ይታገሱ እንዳለን ለቦታው መርጦታል፡፡ እግር ኳስን ከ1990ዎቹ ጀምሮ በድምሩ ለ16 ዓመታት የተጫወተው ይታገሱ አዳማን ጨምሮ ለወንጂ ስኳር፣ መተሐራ ስኳር እና ለሐረር ቢራ ከተጫወተ በኃላ በልጅነት ክለቡ አዳማ ተመልሶ በ2006 ከአንደኛ ሊግ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመለሰ በኃላ እግር ኳስን ማቆሙ ይታወሳል፡፡
ከተጫዋችነት ከተገለለ በኃላ የአዳማ ተስፋ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ወደ ስልጠናው ዓለም ጎራ ያለ ሲሆን በመቀጠል 2011 የፋሲል ከነማ ረዳት ሆኖ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመስራት በ2012 በተመሳሳይ ከአሰልጣኙ ጋር በሰበታ ከሰራ በኃላ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ ከኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱም ጋር በዛው በሰበታ በረዳት አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡
ከሰበታ ከተማ ጋር የነበረው ውል የተጠናቀቀው እና በቅርቡ ከአሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ ጋር የባህርዳር ከተማ ረዳት በመሆን በማምራት ቅድመ ስምምነት የፈፀመ ቢሆንም የአዳማ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች አሰልጣኙ ረዳት ሆኖ እንዲሾሙ ከአሰልጣኙ ጋር ከፍተኛ ድርድር በማድረግ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ለመፈፀም ለአሰልጣኙ ቃል በመግባታቸው የክለቡ ረዳት ለመሆን ወደ አዳማ አምርቷል፡፡