ሀዋሳ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

ትናንት ወደ ዝውውር የገባው ሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውላቸው ተራዝሟል፡፡

ሀዋሳ ከተማ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ በትናንትናው ዕለት ወደ ዝውውሩ በመግባት ፀጋሰው ድማሙን ከሀድያ ሆሳዕና በማስፈረም የሦስት ወጣት ተጫዋቾችን ውል ማደሱ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት የሁለት ተጫዋቾችን ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡

ዳንኤል ደርቤ ውላቸውን ካደሱት መካከል ነው፡፡ ከ1996 ከሀዋሳ ተስፋ ቡድን ካደገ በኋላ በመሐል ለደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ከተጫወተባቸው አራት ዓመታት ውጪ ከአስር ዓመታት በላይ በወጥነት ለሀዋሳ ከተማ የተጫወተው የመስመር ተከላካዩ ሀዋሳን በአምበልነት መምራት የቻለ ሲሆን ባለፈው ሰኔ ወር ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ አሁንም በሀዋሳ ከተማ መለያ ለመቀጠል ውሉን ለተጨማሪ ዓመት በዛሬው ዕለት አራዝሟል፡፡

ሌላኛው ውሉን ያደሰው ኤፍሬም አሻሞ ነው፡፡ ከሙገር ሲሚንቶ የታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኃላ ለሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት፣ ወልዋሎ እና መቐለ 70 እንደርታ የተጫወተው የመስመር አጥቂው መቐለን ከለቀቀ በኃላ በ2013 የውድድር ዘመን በሀዋሳ መለያ ጥሩ ብቃቱን በማሳየት ዓመቱን መፈፀም በመቻሉ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ቢነሳም ለተጨማሪ ዓመት በሀዋሳ ለመቆየት በዛሬው ዕለት ውሉን ማራዘም ችሏል፡፡

ያጋሩ