ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈረመ

ለ2014 የውድድር ዘመን ራሱን እያጠናከረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊው መከላከያ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም የአዳዲስ ፈራሚዎቹን ቁጥር አስር አድርሷል።

ካሰች ፍሰሐ ከሰባት ዓመታት በኃላ ሀዋሳ ከተማን በመልቀቅ ወደ ጦሩ ቤት አምርታለች፡፡ ሲዳማ ቡናን ከለቀቀች በኃላ በግራ እና ቀኝ የተከላካይ ስፍራ በሀዋሳ መለያ ረዘም ያሉ ዓመታትን የደመቀችሁ ፈጣኗ ተጫዋች ሀዋሳን ለቃ አዲስ ክለብ ተቀላቅላለች፡፡

ሀዋሳ ከተማን በመልቀቅ ስድስተኛ፤ መከላከያን የተቀላቀለች ዘጠኛ ፈራሚ ዓይናለም አደራ ነች፡፡ የቀድሞዋ የድሬዳዋ ከተማ የመስመር ተከላካይ በሀዋሳ ከተማ ሦስት የውድድር ጊዜያቶችን ካሳለፈች በኃላ ወደ መከላከያ አምርታለች፡፡

አስረኛዋ የመከላከያ አዲስ ፈራሚ ቤዛዊት ተስፋዬ ነች፡፡ በአማካይ ስፍራ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በዘንድሮው የውድድር አመት ደግሞ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ድንቅ ጊዜን አሳልፋ የነበረችው የመሀል ሜዳ አይደክሜዋ ተጫዋች ከሀዋሳ ጋር ስሟ ሲያያዝ ቢሰነብትም ማረፊያዋ መከላከያ ሆኗል፡፡

የክለቡ አሰልጣኝ መቶ አለቃ ስለሺ ገመቹ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከሆነ የአጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ እና የአምበሏን ፅዮን እስጢፋኖስን ውል ለማራዘም ስለመስማማታቸው ገልጸው ከአስር ዓመታት በኃላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የለቀቀችው አጥቂ ረሂማ ዘርጋውን ለማስፈረም በሒደት ላይ እንዳሉም ጭምር ነግረውናል፡፡