አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ወደ ባህር ዳር ከተማ የሸኘው ሰበታ ከተማ አዲስ አሠልጣኝ ለማግኘት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል።
በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሰበታ ከተማ በቀጣይ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ እስካሁን በይፋ እንቅስቃሴ አልጀመረም ነበር። ከአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር የተለያየው ክለቡም ወሳኝ ተጫዋቾቹን በማጣት ላይ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የክለቡ ቦርድ ትናንት ባደረገው ስብሰባ አዲስ አሠልጣኝ በመቅጠር ወደ ዝውውር ገበያው ለመግባት አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህም የአሠልጣኝ ቅጥር እንዲወጣ ተደርጓል።
ለተወዳዳሪዎች በቀረበው መስፈርት መሠረትም የካፍ A ላይሰንስ ፍቃድ ያለው፣ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የሰራ እንዲሁም በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ ያሰለጠነ የሚሉት እንደተካተቱበት ታውቋል። ተወዳዳሪዎችም እስከ ሐምሌ 17 ድረስ ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቋል።