በቡሩንዲ መሪነት እየተካሄደ የነበረው ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ወደ ነገ ተላልፏል

በምድብ ሁለት የሚገኙት ቡሩንዲ እና ኤርትራ እያደረጉ የነበሩት ጨዋታ በቡሩንዲ መሪነት ቢቀጥልም በስታዲየም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጨዋታው ተቋርጧል።

በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ቡሩንዲ እና ኤርትራ ከ10 ሰዓት ጀምሮ የምድብ ጨዋታቸውን ማድረግ ጀምረዋል። የኤርትራ ሁለተኛ የቡሩንዲ ደግሞ አንደኛ የምድብ ጨዋታ የነበረው ግጥሚያ ከጅምሩ ሙከራዎች የነበሩት ቢሆንም የኋላ ኋላ የጠሩ ጥቃቶች ጠፍቶት ነበር። የሆነው ሆኖ ጨዋታው ገና እንደተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ቡሩንዲዎች በንዱዊማና ፍራንክ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ቢፈፅሙም የግብ ዘቡ ክብሮም ሠለሞን አምክኖባቸዋል። 

ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ቡሩንዲዎች በመጀመሪያ የምድቡ ጨዋታቸው የመጀመሪያ ጎል ቶሎ ለማግኘት መታተር ቀጥለው በ15ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ኒሺሚሪማና ኢስማኤል ከአመቺ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የቀጠሉት ቡሩንዲዎች ሀይል እና ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት በመተግበት ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረዋል። ነገርግን ከመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አጋማሽ ጀምሮ በስታዲየሙ በጣለው ከባድ ዝናብ አጨዋወታቸው ፈተና ተጋርጦበታል። ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት መጫወት የያዙት ኤርትራዎች በበኩላቸው ከቆመ ኳስ ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ፈጣን ሽግግር በማድረግ ወደ ቡሩንዲ የግብ ክልል መሄድ ጀምረዋል። በዝናቡ ምክንያት ውሀ የቋጠረው ሜዳው ግን እነርሱንም እንደልብ እንዲጫወቱ ስላላስቻላቸው ያለ ሙከራ አጋማሹን አገባደዋል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ለመቀጠል ወደ ሜዳ የገቡት የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች ሜዳው እጅግ ውሃ በመያዙ መጫወት አልቻሉም። የዕለቱም ዳኞች ጨዋታው 46ኛው ደቂቃ ላይ እንዲቋረጥ ካደረጉ በኋላም የሚጥለው ዝናብ አለማባራቱን ተከትሎ ጨዋታው ወደ ነገ ረፋድ 5 ሰዓት እንዲተላለፍ ተወስኗል።

ያጋሩ