ወጣቱ የግብ ዘብ ባህር ዳር ከተማን ለመቀላቀል ተቃርቧል

ከጅማ አባጅፋር ጋር ዓመቱን ያሳለፈው ወጣቱ ግብ ጠባቂ የጣና ሞገዶቹን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ከቀጠረ በኋላ ተመስገን ደረሰ፣ መሳይ አገኘሁ፣ ፉአድ ፈረጃ እና አለልኝ አዘነን በእጁ ያስገባው ባህር ዳር ከተማ አምስተኛ ፈራሚ አድርጎ ወጣቱን ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪን በሁለት ዓመት የውል ኮንትራት የግሉ ለማድረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

እግርኳስን በመቱ ከተማ በክለብ ደረጃ በመጫወት የጀመረው እና በክለቡም ሦስት የውድድር ዓመታትን ያሳለፈው ተጫዋቹ በመቀጠል 2012 መስከረም ወር መግቢያ ላይ ወደ ወሎ ኮምቦልቻ አምርቶ እስከ አጋማሹ ድረስ ግልጋሎት ሰጥቷል። ከዛም በጅማ አባ ጅፋሩ የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ መሐመድ ጀማል አማካኝነት በተሰረዘው የውድድር ዓመት መጋቢት ወር ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀለው ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ምንም እንኳን ክለቡ በውጤት የታጀበ ዓመትን ማሳለፍ ባይችልም በግሉ እጅግ አስገራሚ አቅሙን በማሳየት ከበርካቶች አድናቆትን አግኝቶ ነበር፡፡ እርግጥ ተጫዋቹ በቀናት እድሜ ያለው ውል ከጅማ አባጅፋር ጋር እንዳለው ቢታወቅም ነገ አልያም ከነገ በስትያ ከክለቡ መልቀቂያውን ወስዶ ለባህር ዳር ከተማ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።