የሀድያ ሆሳዕና ሥራ አስኪያጅ ከኃላፊነት ተነስተዋል

ሀድያ ሆሳዕናን ረዘም ላለ ጊዜ በሥራ አስኪያጅነት የመሩት አቶ መላኩ ማዶሮ ያስገቡት መልቀቂያ ተቀባይነት በማግኘቱ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

በ2013 የውድድር ዓመት የሀድያ ሆሳዕናን ያህል ስሙ ከተጫዋቾች ውዝግብ ጋር በተደጋጋሚ የሚነሳ ክለብ አልተመለከትንም። አስራ አምስት የክለቡ ተጫዋቾች ከጥቅማ ጥቅም እና ከደመወዝ ጋር በተገናኘ ያቀረቡት ቅሬታ እየከረረ ሄዶ በመጨረሻም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዕግድ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ጭምር ማድረጉ በቅርቡ የተመለከትው ጉዳይ ሲሆን በዚህም የተነሳ የክለቡ የፋይናንስ ኃላፊ ለሁለት ተጫዋቾች በፈረሙት ቼክ መነሻነት ለእስር መዳረጋቸውን እና የክለቡም ሥራ አስኪያጅ በህግ እንደሚፈለጉ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ክለቡን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት አቶ መላኩ ማዶሮ “በክለቡ እየታየ ባለው ክፍተት እና በተደጋጋሚ ለበላይ አካላት በአግባቡም የተጫዋቾቹ ክፍያ እንዲፈፀም ስጠይቅ የሚያዳምጠኝ አካል ሊኖር ባለመቻሉ ከኃላፊነት ልልቀቅ” በማለት ከሰሞኑ ለክለቡ የቦርድ አካላት ያስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት አግኝቶ በዛሬው ዕለት ከአምስት ዓመታት በላይ ያገለገሉበትን መንበር መልቀቃቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ከሥራ አስኪያጁ ስንብት በተጨማሪ በክለቡ ቼክ ላይ ለተጫዋቾቹ ገንዘብ የፈረመው እና በአሁኑ ሰዓትም ለእስር የተዳረገው የክለቡ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ታምሩ ሶደሬ የፈረመው የተቋም ቼክ ላይ እንጂ የግሉ ላይ ባለመሆኑ ክለቡ የህግ ሒደቱን ለመከታተል ብሎም ኃላፊውን ለማስፈታት ዓርብ ዕለት ቀጠሮ መያዙን አረጋግጠናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክለቡ የቦርድ አካላት የ15 ተጫዋቾችን ክፍያ በዚህ ሁለት ቀናት ለመፈፀም ቀጠሮ ስለመያዛቸውም ሰምተናል፡፡