ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በቅርቡ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ውል ያደሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውር ገብቶ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ አስፈረመ፡፡

አጥቂዋ ሰላማዊት ጎሳዬ የመጀመሪያ የክለቡ ፈራሚ ሆናለች፡፡ በመስመር እና በፊት አጥቂነት በጌዲኦ ዲላ ቆይታ የነበራት ተጫዋቿ የደቡቡን ክለብ ለቃ የመዲናይቱን ኢትዮ ኤሌክትሪክን መቀላቀል ችላለች፡፡

ቤቲ ዘውዱ ሁለተኛዋ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ቡድን የተቀላቀለች ተጫዋች ነች፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ፍሬ የሆነቸው አማካይዋ በድሬዳዋ ከተማ በዘንድሮው ዓመት ቆይታ ያደረገች ሲሆን በቅርቡ ወደ መከላከያ ያመራችው ቤዛዊት ተስፋዬን ቦታ ለመተካት ቀይ እና ነጭ ለባሾቹ መቀላቀል ችላለች፡፡

ፀጋ ንጉሤ ሦስተኛዋ የክለቡ ፈራሚ ተጫዋች ሆናለች፡፡ የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዲስ አበባ ተጫዋች በመከላከያ በተከላካይ እና በአማካይ ተከላካይነት ያለፈውን የውድድር ዓመት በመጫወት ካሳለፈች በኃላ ወደ ሌላኛው የአዲስ አበባ ክለብ ኤሌክትሪክ አምርታለች፡፡

መስከረም ኢሳይያስ አራተኛዋ የኤሌክትሪክ አዲሷ ተጫዋች ነች፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ለትውልድ ከተማዋ አርባ ምንጭ ከተማ በተከላካይ ስፍራ ተጫውታ ካሳለፈች በኃላ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ስብስብ ተቀላቅላለች፡፡

ወጣቷ የባህር ዳር ከተማ የቀኝ መስመር ተከላካይ ፀጋነሽ ተሾመ እና የቀድሞዋ የሀዋሳ ከተማ፣ እና አዳማ ከተማ ተጫዋች የነበረችው ባንቺአየው ታደሰም ለክለቡ የፈረሙ አዲስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ያጋሩ