ዋልያው በነገም ጨዋታ የአጥቂውን ግልጋሎት አያገኝም

በኤርትራው ጨዋታ ያልነበረው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ አሁንም ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ባለው የሴካፋ ውድድር የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኤርትራ አቻው ጋር አድርጎ ሦስት ለሦስት መለያየቱ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑ ባሳለፍነው ቅዳሜ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሲያደርግም ጉዳት ላይ የሰነበተው የሀዋሳ ከተማው አጥቂ መስፍን ታፈሰ ከጨዋታው ውጪ ሆኖ ነበር። እርግጥ ተጫዋቹ ካጋጠመው የጡንቻ ጉዳት እያገገመ መሆኑ ቢታወቅም ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ብቁ የሚያደርገው ደረጃ ላይ ባለመገኘቱ በነገው የቡሩንዲ ጨዋታም እንደማይኖር ታውቋል።

መስፍን ብሔራዊ ቡድኑ ባህር ዳር ከገባ በኋላ እስከ ዛሬ ለብቻው ልምምድ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን በሚሰራበት ሰዓት ለብቻው እንቅስቃሴ እየሰራ እንደሆነ ተመልክተናል።