ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ የሚመሩት እና እስከ አሁን አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ሀዋሳ ከተማዎች ሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማከል የአዳዲስ ፈራሚዎችን ቁጥር አስራ አምስት አድርሰዋል፡፡

ሲሳይ ገብረዋህድ ክለቡን የተቀላቀለች አዲሷ ተጫዋች ሆናለች፡፡ በአሰልጣኝ ማህደር እንየው መልማይነት በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ በመሰልጠን የእግር ኳስ ስልጠናውን ዓለም የተቀላቀለችው ወጣቷ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በአካዳሚ በነበራት መልካም እንቅስቃሴ መነሻነት ወደ መከላከያ አምርታ መጫወት የቻለች ሲሆን የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ደግሞ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በተለይ በሁለተኛው ዙር አስገራሚ የሜዳ ላይ አቅሟን በማሳየት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥን ዕድል አግኝታለች፡፡ ውሏ በኤሌክትሪክ የተጠናቀቀው ወጣቷ አማካይ በሁለት ዓመት ውል ወደ ሀዋሳ አቅንታለች፡፡

ሌላኛዋ ፈራሚ ሣራ ነብሶ ነች፡፡ በአጥቂ ስፍራ ላይ ፈጣን ከሚባሉት መካከል አንዷ የሆነችው ሣራ በጌዲኦ ዲላ እና በአዳማ ከተማ ከዚህ ቀደም ተጫውታ አሳልፋለች፡፡ ዘንድሮ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሳለፈችው የመስመር እና የፊት አጥቂዋ ማረፊያዋ ሀዋሳ መሆኑን በፈረመችሁ የሁለት አመት ኮንትራት አረጋግጣለች፡፡

ታዳጊዋ ግብ ጠባቂ እልልታ ጌታቸውም ሀዋሳን ተቀላቅላለች። ከሀዋሳ ከተማ የሴቶች ቢ ቡድን የተገኘችውና የ2013 የውድድር ዓመትን በሁለተኛ ዱቪዚዮኑ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ያሳለፈችው ግብ ጠባቂዋ ወደ አሳዳጊ ክለቧ ተመልሳ ሁለት ዓመታት ለመቆየት ፊርማዋን አኑራለች፡፡

እስከ አሁን አሁን በድምሩ አስራ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው እና የስድስት ነባሮችን ውል ያራዘመው ሀዋሳ ከተማ የአንድ ግብ ጠባቂን ዝውውር ብቻ በቅርቡ ካጠናቀቀ በኃላ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚገባ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡