በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከነገው የቡሩንዲ ጨዋታ በፊት ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው 41ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በዘጠኝ ሀገራት መካከል በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እየተከናወነ ይገኛል። በዚህ ውድድር ላይ እየተካፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም በምድብ ሁለት ከኤርትራ እና ቡሩንዲ ጋር ተደልድሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኤርትራ አቻው ጋር አድርጎ ነጥብ ተጋርቷል (3-3)። በምድብ በሚደረጉ ሁለተኛ ጨዋታዎች ላይ አራፊ የነበረው ቡድኑም በነገው ዕለት የምድብ ጨዋታውን የሚቋጭ ይሆናል።
ከኤርትራው ጨዋታ በኋላ በቀን አንድ ጊዜ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለ ሜዳ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ቡድኑም ዛሬ ከሰዓት ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።
ስምንት ሰዓት ሲል በዝናባማው አየር ለልምምድ ሜዳ የደረሰው ስብስቡም ለ50 ደቂቃዎች ያክል የቆየ ልምምድ ሰርቷል። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ እንደተከታተለችው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ ተጫዋቾቹ እንዲያሟሙቁ ካደረጉ በኋላ ቀላል የኳስ ጋር እንቅስቃሴ ሲያሰሩ ነበር። ኳስን ያማከለ የግል እና የቡድን (አራት ቦታ ተከፍሎ) እንቅስቃሴው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከተከናወነ በኋላም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ያማከለ ጎል የማስቆጠሪያ ሂደት ላይ ያጠነጠነ ስልጠና ሲሰጥ ታዝበናል። በዋናነትም የመስመር ተከላካዮች፣ የአጥቂ አማካዮች እና አጥቂዎች በመናበብ እንዴት ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መግባት እንደሚችሉ አሠልጣኝ ውበቱ ሲያሰሩ አይተናል። ከዚህ በተጨማሪም የመዓዘን ምት ሲገኝ ቡድናዊ እንቅስቃሴን በዋጀ መንገድ ወደ ጎልነት ለመቀየር የሚያስችል ልምምድ ሲሰራ ነበር።
ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስም በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከመስፍን ታፈሰ ውጪ ጉዳት ወይም ህመም ያለበ ተጫዋች አለመኖሩን አረጋግጠናል። በመጀመሪያው የኤርትራ ጨዋታ ያልተሰለፈው መስፍን ታፈሰም ከሰዓታት በፊት በሰራነው ዘገባ እንደገለፅነው ካጋጠመው የጡንቻ ጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ተጫዋቹም ከቡድን አጋሮቹ ተነጥሎ ከዶ/ር ዘሩ በቀለ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአካል ብቃት አሠልጣኝ) ጋር በመሆን ቀላል እና ለቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጁ የሚያደርገውን ልምምድ ሲሰራ አስተውለናል።
ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ በነገው የቡሩንዲ ጨዋታ የቋሚ ተጫዋቾች ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ እየተገመተ ይገኛል። በተለይም በኤርትራው ጨዋታ ድክመት በታየበት የሜዳ ክፍል ላይ ተውጥ እንደሚኖር ተጠብቋል።
የነገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ የሆነችው ቡሩንዲ ዋልያው ልምምዱን ጨርሶ ከስታዲየም ከወጣ በኋላ 9:15 ላይ ልምምድ መስራት ጀምራለች። የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንም በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታው ኤርትራን ገጥሞ ሦስት ለምንም አሸንፎ ነበር። በነገው ጨዋታም ዳግም ሦስት ነጥብ የሚያገኙ ከሆነ የምድቡ የበላይ ሆኖ ወደ ቀጣይ ዙር (ግማሽ ፍፃሜ) የሚያልፍ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ በቀጥታ ወደ ቀጣይ ዙር የሚያሳልፈው ይሆናል።
በአምስተኛ ቀን የሴካፋ ውሎ ነገ አንድ ጨዋታ ብቻ ይደረጋል። በዚህም 10 ሰዓት እንደሚደረግ ቀድሞ ተገልጾ የነበረው የኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ጨዋታ በባህር ዳር አመሻሽ ላይ እየጣለ ባለው ዝናብ ወደ 8 ሰዓት ተለውጧል።