ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች በቀጣይ ዓመት በሊጉ እንዲሳተፉ የተሰጣቸውን ቀነ ገደብ ባለመጠቀማቸው በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደማይሳተፉ ተረጋግጧል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያልተሳተፉት መቐለ 70 እንድርታ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ስሑል ሽረ በቀጣዩ ዓመት የሊጉ ውድድር ተመልሰው የጎደለውን ቦታ እንዲተኩ የመመዝገቢያ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባስቀመጡት ቀነ ገደብም ክለቦቹ ከሐምሌ 1-15 ድረስ ብቻ በውድድሩ የሚሳተፉ ከሆነ እንዲመዘገቡ በደብዳቤ ገልፀው ነበር።
በተቀመጠው ቀነ ገደብም ሦስቱም የክልሉ ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ቢሮ ተገኝተው ምዝገባ እንዳላከናወኑ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ከዚህም መነሻነት ክለቦቹ በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አለመሳተፋቸው እርግጥ ሆኗል። በምትካቸውም ከቀናት በፊት በተከናወነው የማሟያ ውድድር አሸናፊ የሆኑት አዳማ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር እንደሚሳተፉ ታውቋል።
ምናልባት ሦስቱ ክለቦች በቀጣይ ለውድድር የሚመለሱ ከሆነም በኢትዮጵያ የሊግ እርከን ተዋረድ ከክልል ክለቦች ጀምሮ እንዲወዳደሩ እንደሚደረግ ተገልጿል። ምናልባት ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ በልዩ ሁኔታ በሚወስነው ቀጣይ ውሳኔ ተለዋጭ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሰምተናል።