ወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድኑ አሳድጓል

በፕሪምየር ሊጉ የመቆየታቸውን ጉዳይ ያረጋገጡት ወልቂጤ ከተማዎች የአሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ውል ባረዘሙ ማግስት አራት ተጫዋቾችን ከተስፋ ቡድናቸው አሳድገዋል።

ሠራተኞቹ በቀጣይ የውድድር ዘመን ተጠናክረው ለመቅረብ ከወዲሁ ለእድሜ እርከን ቡድኖቻቸው ዕድል በመስጠት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን በአረንጎዴ እና ቢጫ መታወቂያ ማሳደግ ችለዋል።

በአረንጓዴ መታወቂያ ወደ ዋናው ቡድን ያደገው በግራ መስመር የሚጫወተው ቴዎድሮስ ብርሃኑ ሲሆን በቢጫ መታወቂያ ያደጉት ደግሞ በግብ ጠባቂነት ስፍራ የሚጫወተው ቢንያም አብዮት፣ በአጥቂ ስፍራ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ቴፒኒ ፍቃዱ እና ሁለገቡ ተጫዋች ምንተስኖት ዮሴፍ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።

ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት አራቱም ተጫዋቾች በአራት ዓመት ውል መፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።