ከሰዓታት በኋላ ወሳኙን የቡሩንዲ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ቋሚ አሰላለፍ ታውቋል።
በመጀመሪያው የሴካፋ የምድብ ጨዋታ ከኤርትራ አቻው ጋር ሦስት አቻ የተለያየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ 8 ሰዓት የምድብ የመጨረሻ እና ሁለተኛ ጨዋታውን ከቡሩንዲ አቻው ጋር ያደርጋል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በዛሬው ወሳኝ ጨዋታ የመረጡት የመጀመሪያ አሰላለፍም ታውቋል።
አሠልጣኙም ከኤርትራው ጨዋታ አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድ በፋሲል ገብረሚካኤል ሲተካ ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ በመሳይ ጻውሎስ፣ አማካዩ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ በዳዊት ተፈራ እንዲሁም የመስመር አጥቂው ሙኧዲን ሙሳ በብሩክ በየነ ተለውጠዋል። የብሔራዊ ቡድኑ የዛሬ ቋሚ አሰላለፍ የሚከተለው ነው።
በ4-3-3 አሰላለፍ ፋሲል ገብረሚካኤል በግብ ብረቶቹ መካከል ሲቆም ኃይሌ ገብረትንሳኤ፣ መናፍ ዐወል፣ መሳይ ጻውሎስ እና ረመዳን የሱፍ በተከላካይነት ተሰልፈዋል። ዳዊት ተፈራ እና በመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው ዊልያም ሠለሞን ደግሞ ከተከላካዮቹ ፊት የቆመውን ሀብታሙ ተከስተ አጣማሪ ሆነው ተሰልፈዋል። የቡድኑን የፊት መስመር ደግሞ ቸርነት ጉግሳ፣ ብሩክ በየነ እና ሁለት ግቦችን ኤርትራ ላይ ያስቆጠረው አቡበከር ናስር የሚመሩት ይሆናል።