የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 1-1 ቡሩንዲ

እልህ አስጨራሽ ከነበረው እና አንድ አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ውበቱ አባተ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ

ስለ ጨዋታው?

በቅድሚያ የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ጥሩ ጨዋታ ነበር። እቅዳችን ከዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት ነበር። በአጠቃላይ ግን ተጫዋቾቼ ጎሎችን ማስቆጠር ባይችሉም በሜዳ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ደስተኛ ነኝ። ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባን ነበር። ነገር ግን አቻ ተለያይተናል። እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነበር ጨዋታው።

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ስለመዳከሙ

ሁለት አጋማሽ ነበር ለማለት ይከብዳል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃ ትንሽ የማፈግፈግ ነገር ነበር። ይሄ ደግሞ ያገባነውን ጎል አስጠብቆ ከመውጣት ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። ይሄንን በማድረጋችን ደግሞ ተጋጣሚያችን ሰፊ የመጫወቻ ቦታ አግኝተዋል። ከዚህ ውጪ የቆሙ ኳሶችን እንዲያገኙ ፈቅደንላቸው ነበር። ከጎሉ በኋላ ደግሞ እነሱ አፈገፈጉ። እኛ ደግሞ ሦስት ነጥብ ግዴታችን ስለነበር ብዙ የግብ ማግቢያ አማራጮችን ለመጠቀም ሞክረናል። በአጠቃላይ በጨዋታው በነበረችው ያቺ 15 ደቂቃ ይመስለኛል ቡድናችን የተቀዛቀዘው።

ስለ አጠቃላይ ቡድኑ ብቃት?

የዛሬው ጨዋታ ላይ አንድ ጎል ብቻ ስለሆነ የገባው ከማጥቃት ጋር ተያይዞ የነበረውን ነገር ማንሳት አልችልም። ምንም ቢሆን ምንም ግን በጨዋታ አንድ ጎል ማስቆጠር ቀላል ነገር አይደለም። ከሁሉም በላይ ግን ይህ ቡድን ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነው። የኢትዮጵያ ዋናው የወደፊት ቡድን ምን ይመስላል የሚለውን ነው ለማየት እየሞከርን ያለነው። ዛሬ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። በጥሩ ሁኔታም ለማጥቃት ጥረት አድርገናል። ግን በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ መሻሻል እንዳለብን እናምናለን። እግርኳስ የሂደት ውጤት ነው። በአንድ ጊዜ የምትፈልገው ነገር ላይ መድረስ አትችልም። ይህ ቡድን በወራት እድሜ የተገነባ ቡድን ነው እንጂ ከታች ጀምሮ ይዘን የመጣነው አይደለም። ስለዚህ ሁሉንም ነገር በአንድ ጀምበር ካልወለዳችሁ ብሎ ተጫዋቾቹን ማስጨነቅ ከባድ ነው። ግን ያሳዩት ነገር ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።

ጂሚ ንዳይዜዬ – የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማድነቅ እፈልጋለሁ። በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነበር ሲንቀሳቀሱ የነበረው። ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ተጭነውን ነበር ሲጫወቱ የነበሩት። የመጀመሪያውን ጨዋታ በማሸነፋችን እኛ ዛሬ ጫና ውስጥ ገብተን ነበር። ግን የኢትዮጵያ ቡድን በጣም ምርጥ ቡድን ነው። በአጠቃላይ ግን እኛ አንድ ነጥብ ለማግኘት የሚያስችለንን ሥራ ሰርተን ከሜዳ ወጥተናል።

ስለ ቀጣዩ የኬንያ ጨዋታ…?

የኬንያ ብሔራዊ ቡድንን አይቼዋለሁ። ጥሩ ቡድንም ነው። በጣም ቴክኒካል ተጫዋቾችም አሉት። ከዚህ በተጨማሪም በአካላዊ ቁመናም ገዘፍ ያሉ ናቸው። ግን ከግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ በፊት ሁለት ቀናት ስላሉን በደንብ ተዘጋጅተን ለጨዋታው እንቀርባለን።