የሴካፋ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው አቡበከር ናስር የተሰማውን ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርቷል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሁለት ሳምንታት በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የ2021 የሴካፋ ዋንጫ ከሰዓታት በፊት በታንዛንያ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወቃል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ዝቅተኛ ቢሆንም የብሔራዊ ቡድን አምበል አቡበከር ናስር የሴካፋ ውድድር ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። ይህ ክብር ከዚህ ቀደም በ2008 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተደረገው የሴካፋ ውድድር (በዋና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ) ኤልያስ ማሞ በተመሳሳይ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ይታወሳል።
የኮከብ ሽልማቱ ሲበረከትለት በአካል ያልነበረውን እና ሽልማቱን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ አስራት አባተ አማካኝነት የተቀበለው አቡበከርን በስልክ ደውለን ስለተሰማው ስሜት አናግረነው ተከታዩን ብሎናል።
“ኮከብ ተጫዋች ተብዬ እመረጣለሁ ብዬ አልጠበኩም። መስዑድ መሐመድ ነው ሶከር ኢትዮጵያ ላይ አይቶ የነገረኝ። ኮከብ ተብዬ በመመረጤ በጣም ደስ ብሎኛል። ይህ ዓመት የእኔ ነው ማለት ይቻላል። ያው በሴካፋ ውድድር ሀገራችን ጥሩ ቡድን ይዛ ቀርባ ነበር። ጥሩ ስብስብ ነበረን። ሆኖም ጥሩ ነገር አልሰራንም። ዋናው እቅዳችን ዋንጫ ማግኘት ነበር። ብዙዎቻችን ለውድድሩ አዲስ በመሆናችን የከበደን ይመስለኛል። በሴካፋ የተሳተፉ ሌሎቹ ሀገራት ከ17 ዓመት በታች ጀምሮ አብረው የመጡ መሆናቸው እና እኛ ሀገር ይህ ስላልተለመደ ውጤታማ ሳንሆን ቀርተናል እንጂ በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። ውድድሩም ቀላል ነበር። ያም ቢሆን እኔ በግሌ ኮከብ በመባሌ በጣም ደስ ብሎኛል። በቡድን አጋሮቼ እና አሰልጣኞቼ እገዛ የመጣ ስኬት በመሆኑ እነርሱን አመሠግናለው።”