የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በቀጣዩ ዓመት በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል እንዲደረግ ተወሰነ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ2014 የውድድር ዘመን በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዓመት በ11 ክለቦች መካከል መደረግ ሲገባው የትግራይ ክልል ተወካይ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ ሳይካፈል በመቅረቱ በአስር ቡድኖች ተካሂዶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቻምፒዮን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ልማት ኮሚቴ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከተጠናቀቀ በኃላ ለቀጣዩ የ2014 የሊግ ውድድር የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ ሲሆን ከእነዚህም አንዱ በመጪው ዓመት ተሳታፊ የአንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦችን ቁጥር መጨመር ነው። በዚህም ተጨማሪ ክለቦች በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ዘጠነኛ እና አስረኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርደው የነበሩት አርባ ምንጭ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከወረዱበት በድጋሚ ተመልሰው በአንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ እንዲቀጠሉ ሲወሰን በሁለተኛ ምክንያት ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ዕድልን ያገኘው ባህር ዳር ከተማ እና ቦሌ ክፍለ ከተማን ተከትሎ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቆ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የመጨረሻ ጨዋታ ሲደረግ ሻሸመኔ ከተማ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፎርፌ በመስጠቱ በወቅቱ የፈረሰኞቹ እንስቶች ክለብ የማደግ ዕድል እያለው በተሰጠው ፎርፌ ዕድሉን ያጣ በመሆኑ እና የመቐለ 70 እንደርታ የሴቶች ክለብ በቀጣዩ ዓመት የማይሳተፍ በመሆኑ ዕድሉን ሊያገኝ እንደቻለም አረጋግጠናል፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የሚሳተፉ ክለቦች አስራ ሶስት ደርሰዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መከላከያ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጌዲኦ ዲላ፣ አዳማ ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ባህር ዳር ከተማ ፡ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2014 ተሳታፊ ክለቦች ይሆናሉ፡፡

በተያያዘ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ የሆነው የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ክለብ ለቀጣዩ አመት ሰልጣኝ ስፖርቶኞች በአካዳሚው አለመኖራቸውን ተከትሎ ቀጣይ ዓመት ተሳታፊ አለመሆኑን አረጋግጠናል፡፡ በዚህም መሠረት ቀሪ የዲቪዚዮኑ ክለቦች ቁጥራቸው ወደ ስድስት ዝቅ ያለ ሲሆን በነገው ዕለት በሀዋሳ በሚጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሁለት ምድብ ተደርጎ የሚደረግ ሲሆን በሁለቱም ምድብ ከአንድ እስከ አራት የሚወጡ ስምንት ቡድኖች ወደ 2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን በማደግ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ወደ አስራ አራት ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርደው የነበሩት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ በተሳታፊነታቸው ይቀጥላሉ፡፡