የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ነገ ይካሄዳል

ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የሚያድጉ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ ለመግባት የሚደረገው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዕጣ ማውጣት መርሐግብር ነገ ውድድሩ በሚደረግበት ሀዋሳ በይፋ ይወጣል፡፡

የ2013 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በበርካታ ክለቦች መካከል በሁለቱም ፆታ ከፊታችን ዕሁድ ሐምሌ 18 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት በይፋ ይጀመራል፡፡ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በአካባቢያቸው ባደረጉት የውስጥ ውድድር መሠረት በወንዶች ከአንድ እስከ አምስተኛ የወጡ ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በድምሩ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ቀደም ብሎ እንሳተፋለን ያሉ ቡድኖች ቁጥራቸው 55 ደርሷል። ወደ 2014 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ለማለፍ በሚደረገው ውድድር ላይ ተካፋይ ለመሆን ግን እስከ አሁን 46 ቡድኖች ብቻ መመዝገባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ከትግራይ ክልል ውጪ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ ክለቦች በሚካፈሉበት በዚህ ውድድር ላይ ምናልባትም ከጠቀስነው ቁጥር ውጪ እስከ ነገ ድረስ የመመዝገቢያ 50 ሺህ ብር ክፍያን የሚፈፀሙ ከሆነ ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በሴቶች በሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ እስከ አሁን አስራ ሁለት ቡድኖች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን ውድድሩም የፊታችን ዕሁድ የሚጀመር ይሆናል፡፡ ከጨዋታው ቀደም ብሎ የሚደረገው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት በነገው ዕለት ቅዳሜ በ9፡00 በሀዋሳ ሲዳማ ባህል አዳራሽ የክለብ ተወካዮች የፌድሬሽን አመራሮች እና ሌሎችም በተገኙበት የሚከናወን ይሆናል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ከነገው የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ጀምሮ ውድድሩንም ጭምር ወደእናንተ የምታደርስ ይሆናል፡፡