ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚያልፉ ክለቦችን ለመለየት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በአስር ክለቦች መካከል የፊታችን ሰኞ መደረግ ይጀምራል፡፡
የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሚል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ መደረግ ይጀምራል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚያድጉ ቡድኖችን ለመለየት የሚደረገው ይህ ውድድር በአስር ክለቦች መካከል ከፊታችን ሰኞ ሐምሌ 19 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ መደረግ የሚጀምር ይሆናል፡፡
ውድድሩን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንም በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ የክለብ ተወካዮች በተገኙበት የዕጣ ማውጣት መርሀግብር እና የደንብ ውይይቶችን አከናውኗል፡፡ አቶ ጌታቸው የማነ ብርሀን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሴቶች ልማት ኮሚቴ እና የውድድሩ ሰብሳቢ ስለ ውድድሩ አላማ አስረድተው ሁሉም ክለቦች ለሴት እግር ኳስ ትኩረት ሰጥተው ለመሳተፍ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ከገለፁ በኃላ ለውድድሩ የቀረበውን ደንብ ማብራራሪያ ሰጥተው ክለቦችም ጥያቄዎችን በቀረበው ደንብ ላይ በመወያየት አፅድቀውታል፡፡
ከደንቡ በመቀጠል አቶ ጌታቸው ለውድድሩ ስድስት ዋና እና ስድስት ረዳት ዳኞች እንደተመደቡ ገልፀው ለውድድሩ ትኩረት በመስጠትም ኢንተርናሽናል እና ሲኒየር ፌድራል ዳኞች እንደተመደቡ እና አራት ኮሚሽነሮችም ለውድድሩ ሀዋሳ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ አስር ቡድኖችን የሚያካፍለው ይሄ ሻምፒዮና በሁለት ምድቦች የተከፈለ ሲሆን ከሁለቱም ምድብ ከአንድ እስከ አራት የሚወጡ በድምሩ ስምንት ክለቦች ወደ 2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚያድጉም ይሆናል፡፡ ውድድሩ የፊታችን ሰኞ በሚደረግ ሁለት መርሀግብር የሚጀመር ሲሆን በወንዶች ከሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ጎን ለጎን የመወዳደሪያ ሜዳዎች እና ሰአት በነገው ዕለት የሚገለፅ ይሆናል፡፡
ምድብ ሀ
ሰበታ ከተማ (ከኦሮሚያ ክልል)
አራዳ ክፍለ ከተማ (ከአዲስ አበባ)
ወላይታ ዞን (ከደቡብ ክልል)
ሀላባ ከተማ (ከደቡብ ክልል)
ምስራቅ ክፍለከተማ (ሀዋሳ ሲዳማ)
ሰኞ በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ
አራዳ ክፍለ ከተማ ከ ምስራቅ ክፍለ ከተማ
ወላይታ ዞን ከ ሀላባ ከተማ
ምድብ ለ
አሰላ ከተማ (ከኦሮሚያ ክልል)
ከንባታ ዞን (ከደቡብ ክልል)
አለታ ወንዶ ከተማ (ከሲዳማ ክልል)
ሱሉልታ ከተማ (ከኦሮሚያ ክልል)
ፔንዳ ክለብ (ከአዲስ አበባ ከተማ)
በተመሳሳይ ከዚህ ምድብ ሰኞ ነገ በሚገለፅ ሜዳ እና ሰዓት መሠረት
ከንባታ ዞን ከ ፔንዳ ክለብ
አለታ ወንዶ ከተማ ከ ሱሉልታ ከተማ የሚየጫወቱ ይሆናል፡፡