በደረጃ ጨዋታ ኤርትራ ኢትዮጵያን አሸንፋለች

ደረጃ ለመለየት የተደረገው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨዋታ ኤርትራን በመለያ ምት አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

በውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ ኤርትራን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡሩንዲው ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጎ ጨዋታውን ቀርቧል። በዚህም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ኃይሌ ገብረትንሳኤን በአሥራት ቱንጆ፣ ሀብታሙ ተከስተን በበረከት ወልዴ እንዲሁም በሁለት ቢጫ ያረፈው ዊልያም ሰለሞንን በወንድማገኝ ኃይሉ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 25 ደቂቃ ድረስ የሰላ ሙከራ አልተስተናገደበትም ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግን በተሻለ ኳስን በመቆጣጠር ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥር የኤርትራ ተጫዋቾች ደግሞ ከኳስ ጀርባ በመሆን መንቀሳቀስን መርጠዋል። በዋናነት በተጠቀሰው አጨዋወት በመጫወት የሚያገኙትን ኳስ ግን በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ፊት ሲያደርሱ ታይቷል።

በ25ኛው ደቂቃ ግን በጨዋታው የተስተናገደው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ ግብነት ሊቀየር ከጫፍ ደርሶ ነበር። በዚህ ደቂቃም ዳዊት ተፈራ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂውን ያለፈውን ኳስ ናሆም ዐወት እንደምንም ዘሎ ከመስመር ላይ አድኗታል።

ይሄን ሙከራ ያስተናገዱት ኤርትራዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የቆመን ኳስ መነሻ ያደረገ ዕድል አግኝተው ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ሰጥተዋል። ከወደ ቀኝ የተሻማው የቅጣት ምት በአግባቡ ሳይፀዳ እግሩ ስር የደረሰው አብሌሎም ተክለዝጊይም ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል ተቆጣጥሮበታል።

ጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም ዋልያው ሌላ ያለቀለት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። በዚህም ወንድማገኝ ኃይሉ በቀኝ መስመር ሰብሮ ገብቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። አሁንም በፈጣን ሽግግር የኢትዮጵያ የግብ ክልል የደረሱት ኤርትራዎች በዓሊ ሱሌይማን የግል ጥረት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ የወሰዱትን ብልጫ በጎል ለማሳጀብ የፈለጉት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች ግብ ሊያስቆጥሩ ተቃርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ብሩክን ቀይሮ የገባው ሙኽዲን ረመዳን ታግሎ የሰጠውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ለጥቂት ወጥቶበታል። አጋማሹም ያለ ጎል ተጠናቋል።

በሁለተኛውም አጋማሽ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የያዙት ዋልያዎቹ በ47ኛው ደቂቃ የአጋማሹን የመጀመሪያውን ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህም ከመስመር የተነሳውን ኳስ ቸርነት ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኤርትራዎች ከጥሩ ቦታ ያገኙትን የቅጣት ምት በናሆም ታደሠ አማካኝነት መረብ ላይ ሊያሳርፉት ተቃርበው ነበር።

የኋልዮሽ እና የጎንዮሽ ኳሶችን በማዘውተር መጫወት የቀጠሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጠጣሩን የኤርትራ የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸው 77ኛው ደቂቃ ደርሷል። በተጠቀሰው ደቂቃ ግን በረከት ወልዴ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ጥሩ ኳስ ቢሞክርም ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው አምክነውበታል። በሚገርም መታተር የሚጫወቱት ኤርትራዎች ግን በ81ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ጎል በፈጣን ሽግግር አግኝተዋል። በዚህም ዓሊ ሱሌይማን ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ፋሲል ጀርባ በሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ጭማሪ ደቂቃ በሚያሳዩበት ቅፅበት አቡበከር ናስር ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። መደበኛው ጨዋታም አንድ አቻ ተጠናቆ አሸናፊዎቹን ለመለየት የመለያ የፍፁም ቅጣት ምት መመታት ተጀምሯል። በተመቱት የመለያ ምቶችም የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን 3-2 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አምስተኛ ደረጃን ለመያዝ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ዩጋንዳ አሸናፊ ጋር ከነገ በስትያ የሚጫወት ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ዩጋንዳ ተሸናፊ የሚገጥሙ ይሆናል።