ደረጃ ለመለየት ከተከናወነውና ኤርትራን በመለያ ምት አሸናፊ ካደረገው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥተዋል።
ዳንኤል ዮሐንስ – የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ቴክኒካል ዳይሬክተር
ስለጨዋታው…?
በጨዋታ ቁጥጥር የተሻልን ነበርን ፤ ውጤቱም ወደእኛ መጥቷል። ክፍተቶችን ላለመፍጠር እና ላለመቸገር መከላከልን መርጠን ተጫውተናል። ያም ደግሞ ወደ መለያ ምት እንድንደርስ ረድቶናል። የመለያ ምት ደግሞ ከታክቲካል ዝግጅት ይልቅ ዕድልን መሰረት ያደረገ ነው። የዛሬው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን ኳስ የተቆጣጠረበት ነገር ግን ውጤት ያላገኘበት ነው። በመከላከል ላይ የተመሰረተው የኤርትራ ቡድን ደግሞ ውጤቱን ያገኘበት ነው። ውጤቱን ለማግኘት የተሻለ ታክቲካዊ ብልጫ የወሰድንበት ጨዋታ ነበር።
ስለአጨዋወታቸው…?
ኳስ የሚወሰነው በውጤት ነው። እኛ የሚያዋጣን ጨዋታ ምን እንደሆነ በማሰብ ገብተናል። ውጤቱም አጨዋወታችን እንዳዋጣን አሳይቷል። ጨዋታ ኳስ በመያዝ ብቻ የሚወሰን ቢሆን ኖሮ ጎልም አያስፈልግም ነበር። ኳሱን ለያዘው ውጤቱን መስጠት ይቻል ነበር። ስለዚህ እኛ የሚያዋጣንን ነው ያደረግነው። ባዋጣንም ደግሞ ውጤት አግኝተናል በጣም ደስተኞች ነን።
አጨዋወታቸው ከዚህ ቀደም ከነበረው ሰለመለወጡ…?
በኳስ ይበልጡናል። በእንቅስቃሴ ፈጣን ስለሆኑ ከተጋጣሚያችን አንፃር የመከላከል እግር ኳስን ከማን ጋር ነው የምንጫወተው የሚለውን መለየት አለብን። እንደባህል እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምንጫወት ቢሆንም ለዚህ ጨዋታ የሚሻለንን አጨዋወት መምረጥ ነበረብን። ለአንድ ጨዋታም ቢሆን ምርጫችንን ማስተካከል ነበረብን። ለዚህ ነው መከላከልን መርጠን ውጤታማም ልንሆን የቻልነው።
ስለውጤቱ ፋይዳ…?
በዚህ ጨዋታ ማሸነፋችን ለቡድኑ መነቃቃት እና ለእግር ኳሳችን ዕድገት በር ይከፍታል ብዬ አምናለሁ።
ውበቱ አባተ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
ስለጨዋታው…?
በቅድሚያ ለኤርትራ ብሔራዊ ቡድን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በሙሉው ጨዋታ ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት እና ወደ ኋላ የተሳበውን የኤርትራ ቡድን ሰብረን ለመግባት ጥረት አድርገናል። ነገር ግን ከተጋጣሚህ የተሻለ ማስቆጠር ካልቻልክ አታሸንፍም። ነገር ግን በቡድናችን ላይ መሻሻል እያየን ነው ፤ በተለይ ኳስ በመቆጣጠር እና ዕድሎችን ለመፍጠር በመሞከር በኩል። ነገር ግን አንዳንዴ ከርቀት መሞከርም ይኖርብናል። በመጨረሻው የጨዋታ ሂደት ላይ ብዙ መሻሻል አለብን ፤ ያ ጨዋታውን ወስኖታል። በአጠቃላይ ግን ጥሩ ለመጫወት ሞክረዋል። እንደአጋጣሚ ሆኖ ጨዋታውን ለማሸነፍ ዕድለኛ አልነበርንም።
ስለቡድኑ የአጨራረስ ችግር…?
እንዳያችሁት ለራሳችን አንድ እየገነባን ያለነው ነገር አለ። በአካል ብቃት ላይ ካተኮሩ ቡድኖች ጋር እነሱ በሚጫወቱበት መንገድ ተጫውተን ኳሱን የጋራ አድርገን መብለጥ አንችልም። በእንቅስቃሴ መብለጥ ጨዋታውን መቆጣጠር መቻል፣ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ብዙ ቀርበን መጫወት፣ ተከላካይ ክፍላችንን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተን መጫወት እነዚህ ቡድኑ ላይ የታዩ ዕድገቶች ናቸው። በመጨረሻ ግን በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ሰብረን ገብተን ወደ ግብ መምታት እና ማስቆጠር አለብን። እዛ ላይ የበለጠ መሥራት አለብን። ነገር ግን እንደ ቡድን ባህል ማንም ቡድን ኢትዮጵያ ሲባል ምን ዓይነት አቀራረብ አለው ከሚለው አንፃር የራሳችንን ባህል እየፈጠርን ይመስለኛል።
ስለተጋጣሚያቸው…?
ዛሬ በጣም ጠጣር ነበሩ። ወደ ግባቸው ቀርበው ነው የሚጫወቱት። እንደውም ባለፈው በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ፤ እኛ ኳስ ይዘን ለመቀባበል እንሞክር እንጂ ግልፅ የግብ ዕድል በመፍጠር ከዛሬው ጨዋታ ይልቅ ባለፈው የተሻሉ ነበሩ። ዛሬ ላይ በጣም ወደ ጎላቸው ቀርበው ግባቸውን በቀላሉ እንዳናገኝ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ያ የመከላከል ሰንሰለታቸው ጠንካራ ነበር ብዬ መናገር ነው የምችለው።
ከሦስቱ ጨዋታዎች ለዋናው ቡድን ተስፋ ስለማየታቸው…?
የምንሰራው አንድ ዋናውን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ነው። እሱን ለመገንባት እላይ ያለው የብሔራዊ ቡድኑ የአጨዋወት መንገድ ከታችኞቹ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ነው ጥረት እያደረግን ያለነው። አሁንም ቢሆን ከጥራት መለያየት ውጪ ያንኑ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉልን እየሰራን ነው። ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ልጆችንም እያየን ነው። እንግዲህ ከእነዚህ ተጫዋቾች ቢያንስ ሰባ በመቶው የቀጣዩ ስምንት ዓመት ቡድን የምናገኝ ይመስለኛል። ያን ቡድን ከመገንባት አንፃር ጥሩ ሥራ እየሰራን ነው ብዬ ነው የማስበው።