በሲዳማ ቡና ቀሪ የአንድ አመት ውል የነበራቸው ሁለት ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል፡፡
በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በዛሬው ዕለት ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ባደረገው ስምምነት መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለቱም አካላት አረጋግጣለች፡፡ ከክለቡ ጋር ውል እያለው የተለያየው አንደኛው ተጫዋች ፈቱዲን ጀማል ነው፡፡ የቀድሞው የሀላባ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ፈቱዲን ኢትዮጵያ ቡናን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከለቀቀ በኃላ የቀድሞው ክለቡ ሲዳማ ቡናን በይፋ በሁለት ዓመት ውል መቀላቀል የቻለ ሲሆን ከክለቡ ጋር ይቀጥላል ተብሎ ሲጠበቅ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያለው ከክለቡ ጋር ባደረገው ስምምነት በዛሬው ዕለት የውል ማፍረሻ በመክፈል ተለያይቷል፡፡
ሌላኛው ከክለቡ የተለያየው አበባየው ዮሐንስ ነው፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አበባየው ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት ደቡብ ፓሊስን ከለቀቀ በኃላ በሲዳማ ቡና ቤት በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ልክ እንደ ፈቱዲን ሁሉ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው በስምምነት የውል ማፍረሽያ በመክፈል በአካል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በመገኘት ውሉን ከሲዳማ ቡና ጋር አቋርጧል፡፡
ከሲዳማ ቡና ጋር በዛሬው ዕለት የተለያዩት ሁለቱ ተጫዋቾች ከሦስት ክለቦች ጋር ድርድር እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ አልያም ነገ ወደ አዲስ ክለብ ሊያመሩ እንደሚችሉ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡