በሴካፋ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ታንዛኒያ እና ቡሩንዲ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያን በማሸነፍ ለፍፃሜ አልፈዋል።
👉ታንዛኒያ 1-0 ደቡብ ሱዳን
ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው ሙከራ የተስተናገደበት በ12ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃም የታንዛኒያ ተጫዋቾችን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ የደቡብ ሱዳኑ አጥቂ ዳኒ ሉዋል ጉማኖክ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። ይህ የሰላ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ታንዛኒያዎች ቀስ በቀስ ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ እድገት ቢያሳዩም እስከ 30 ደቂቃ ድረስ አንድም የጠራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
ደቡብ ሱዳኖች ግን በጥሩ ታክቲካል ዲሲፕሊን ክፍተቶችን በመዝጋት እንደ አስፈላጊነቱ ብቻ ኳስን እየተቆጣጠሩ መጫወትን መርጠዋል። በ26ኛው ደቂቃ ደግሞ ሁለተኛ ሙከራቸውን በስቴፈን ፓዋር ሎኒ አማካኝነት በመሰንዘር መሪ ለመሆን ሞክረው መክኖባቸዋል። እንደተጠቀሰው ታንዛኒያዎች በ30ኛው ደቂቃ ሪሊያን ምዋካሳጉሌ ከሳጥኑ ጫፍ ሆነ በሞከረው ነገርግን ዒላማውን በሳተው ኳስ ጥቃት ፈፅመዋል። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላም ዳግም ደቡብ ሱዳኖች በስቴፈን ሎኒ ሌላ ያለቀለት ሙከራ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ተጫዋቹ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ከመዓዘን ሲሻማም ዋኒ ኢቫን አዴቦ አግኝቶት ሞክሮት ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ታንዛኒያዎች አንድሪው ሲንቺምባ ከወደ ግራ መስመር ባዘነበለ ቦታ ባገኘው እና በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ሊቀይረው በዳዳው ኳስ መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ነበር። ነገርግን ኳሱን የግብ ዘቡ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል። አጋማሹም ያለ ጎል ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽን ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ ሻል ብለው የቀረቡ የሚመስሉት ደቡብ ሱዳኖች የሚያገኟቸውን ኳስን በፍጥነት በመቀባበል ታንዛኒያዎች ላይ ጫና ማሳደር ይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን ጥሩ በሆኑባቸው ደቂቃዎች መልካም የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል። ታንዛኒያዎች በበኩላቸው ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር ቀዳሚ ለመሆን ሲታትሩ ነበር። በ61ኛው ደቂቃም ምዋካሳጉሌ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡድኑ ያገኘውን የቅጣት ምት በኬልቪን ናፍታል አማካኝነት ወደ ጎልነት ቀይሮ የልፋቱን ፍሬ በማግኘት መሪ ሆኗል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ታንዛኒያዎች ተጨማሪ ግብ በማግባት መሪነታቸውን ለማስፋት በመፈለግ ተንቀሳቅሰዋል። ደቡብ ሱዳኖች ግን በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ያሳዩትን ብልጫ ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል። እርግጥ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቡድኑ ጫና በመፍጠር የአቻነት ጎል ለማግኘት ቢፍጨረጨርም ውጥኑ መና ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም የጨዋታው አሸናፊ ታንዛኒያ የፊታችን ዓርብ ሁለተኛውን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ካሸነፈቸው ቡሩንዲ ጋር የፍፃሜ ጨዋታዋን የምታደርግ ይሆናል። ተሸናፊዋ ደቡብ ሱዳን ደግሞ ከኬንያ ጋር ለደረጃ ትፋለማለች።
👉ቡሩንዲ 0-0 (4-2) ኬንያ
መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ማስመልከት የጀመረው የቡሩንዲ እና ኬንያ ጨዋታ ጅማሮው ላይ እምብዛም ለዐይን ሳቢ አልነበረም ነበር። ቡድኖቹም ቶሎ ቶሎ ኳስ እየተነጣጠቁ 20ኛው ደቂቃ ደርሷል። በዚህ ደቂቃ ግን የኢትዮጵያ አቻቸውን አሸንፈው ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀሉት ቡሩንዲዎች ቀዳሚ ሊሆኑ ከጫፍ ደርሰዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሰው ቡድኑም ንሺሚሪማና ኢስማኤል ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ የኬንያን መረብ ለማግኘት ጥረዋል።
በአንፃራዊነት ኳሱን በመቆጣጠሩ ረገድ ደቂቃ ከደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ኬንያዎች በ28ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረበ የመጀመሪያ ሙከራቸውን በጆስፋት ሎፓጋ አማካኝነት ሰንዝረው ነበር። ነገርግን ሎፓጋ ከወደ ቀኝ ባደላ ቦታ የመታው ኳስ ለጥቂት ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ሙከራ ሳይስተናገድ ተጫዋቾች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ፉክክሩ ወርዶ የቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽም ከጠሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች የራቀ ነበር። በአጋማሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሳ ሙከራ ያደረገችው ቡሩንዲ ግን በ57ኛው ደቂቃ ንዲኩማና አስማን ከግራ ተሻምቶለት በጭንቅላቱ በሞከረው ኳስ ኬንያን አስደንግጣለች። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ንሳቢማና ሁበርት በሞከረው የቅጣት ምት ሌላ ጥቃት ሰንዝራለች።
ትንሽ ሻል እያለ የመጣው ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጠንከር ለማለት የሞከሩት ኬንያዎች ተቀይረው የገቡት ንጁጉና ኮሊንስ እና ኦሎች ኦቺንግ ተናበው ሳጥን ውስጥ በመገኘት ባገኙት ወርቃማ ዕድል ግብ ሊያስቆጥር ነበር። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ በሌላኛው ተቀይሮ በገባው የመስመር አጥቂ ኦኮት ዴቪድ ኦዲሂያምቦ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የቡሩንዲው አምበል እና የግብ ዘብ ሩኩንዶ ዋንሲሚ አክሽፎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝ ተጫዋች ጠፍቶ አላፊውን ቡድን ለማወቅ የመለያ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷል። በመለያ ምቶቹም ቡሩንዲ 4-2 አሸንፋለች።
ቡሩንዲ ይህንን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ማሸነፏን ተከትሎ ከታንዛኒያ ጋር የፍፃሜ ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን ኬንያ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ከደቡብ ሱዳን ጋር የምትጫወት ይሆናል።