ቅዱስ ጊዮርጊስ ከብራዚሉ ክለብ ጋር በጋራ ለመሥራት ተስማማ

ሁለቱ ረጅም የምስረታ ዕድሜ ያላቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኮረንቲያስ ክለብ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እንደፈፀሙ ክለቡ ይፋ አድርጓል፡፡

ክለቡ በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ክለቦች ጋር የልምምድ ልውውጥ እና በጋራ የመስራት ዕቅድ የነበረው ሲሆን ይሄንንም ዕቅዱን በዛሬው ዕለት ከብራዚሉ ኮረንትያስ ክለብ ጋር አድርጓል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረመስቀል እና የክለቡ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት እንዲሁም ደግሞ የኮረንቲያስ ክለብ ተወካይ ፓውሎ ፓን እና ሌሎች አካላት በተገኙበት ነው ይሄ ስምምነት የተፈፀመው።

በስምምነቱ ፈረሰኞቹ የአንድ መቶ አስራ አንድ አመት ዕድሜ ካለው ክለብ ጋር በተጫዋች አሰለጣጠን ፡ በክለብ አስተዳደር ፡ በታዳጊዎች የስልጠና ሂደት ፡ የእግር ኳስ ፍልስፍና አተገባበር ፡ በቢዝነስ እና ማርኬቲንግ እንዲሁም የደጋፊዎች አያያዝን የተመለከተ ስምምነት እንደፈፀሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይፋ አድርጓል፡፡

በሁለቱ ክለቦች መካከል በአዲስ አበባ እና በሳኦፓውሎ የወዳጅነት ጨዋታዎች በማድረግ በእግር ኳሱ ዘርፍ የትብብር ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ስለሚቻልበት ጉዳይም ሰፊ የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓልም ተብሏል፡፡

ያጋሩ