ዋልያው በሴካፋ ውድድር ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል

በሴካፋ ውድድር ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የተደረገው የኢትዮጵያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተደምድሟል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ዋልያዎቹ በቅድሚያ ጠንከር ያለ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ነበር። በዚህም ጨዋታው በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ምፒያ ማክሲ ሳጥኑ ጫፍ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶታል።

በቀጣይ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የግብ ክልል የደረሱት ዋልያዎቹ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በመጀመሪያ ሙከራቸው ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህም ዊልያም ሰለሞን ከግራ መስመር እየገፋ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ መነሻ ባደረገ ዕድል ወደ ግብ የተመታው ኳስ የኮንጎ ተከላካዮች ከመስመር ሲመልሱት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አሥራት ቱንጆ አግኝቶት ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ13ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ ሊያገኝ ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃም ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ኮንጎዎች ኢካንጋ ጆናታን ከግራ መስመር ተሻግሮለት በግንባሩ በሞከረው ኳስ ጥቃት ሰንዝረው መክኖባቸዋል።

ጨዋታው ቀጥሎ በማጥቃቱ ረገድ ከሌላው ጊዜ ሻል ብለው የታዩት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች በ22ኛው ደቂቃ 22 ቁጥር መለያ ባደረገው ቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ባገኙት ሁለተኛ ጎል መሪነታቸውን አስፍተዋል።

በቀጣዩ ደቂቃ ግብ የሚያገኝ የሚመስለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ28ኛው ደቂቃ ዊልያም ታትሮ በመሮጡ ባገኘው ነገርግን ለጥቂት ዒላማውን በሳተበት አጋጣሚ ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ከጫፍ ደርሶ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ በጨዋታው ደከም ብለው የታዩት ኮንጎዎች ቀይረው ባስገቡት ቤያ ጆይል አማካኝነት እጅግ የሰላ ጥቃት ፈፅመው ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ አቡበከር ከዊልያም የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ቢመታውም የግብ ዘቡ ኢፎንጊ ብሩዴ መልሶበታል።

ቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የያዙት ኮንጎዎች የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተጭነው መጫወት ጀምረዋል። በዚህም በ54 እና 55ኛው ደቂቃ ኪካሳ ማርቪሌ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተገኝቶ አከታትሎ ጥሩ ሙከራ ሞክሮ ነበር። አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ኮንጎዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ያሳዩትን ጠንካራ እንቅስቀሴ በ60ኛው ደቂቃ በጎል አሳጅበዋል። በዚህም ኪምቩይዲ ካሪም ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰች ጎል አስቆጥሯል።

ያገኙትን ሦስት ነጥብ ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወት የመረጡት ዋልያዎቹ አሁንም ጥቃት ማስተናገድ ቀጥለዋል። በ78ኛው ደቂቃም ማዋዉ ኦርቲኔል ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን የቅጣት ምት መረብ ላይ ለማሳረፍ ቢዳዳም ፋሲል ገብረሚካኤል ሙከራውን አክሽፎበታል። አሠልጣኝ ውበቱም የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲጥሩ ታይቷል።

ጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ላይም ሙከራዎች መስተናገድ ቀጥለዋል። በቅድሚያም የዋልያው አምበል አቡበከር በግራ መስመር የደረሰውን ኳስ በማስቆጠር ቡድኑ ላይ የነበረውን ጫና ለማቀዝቀዝ ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የኮንጎው አጥቂ ኪምቩይዲ ካሪም ከርቀት ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ቡድኑን አቻ ለማድረግ ሞክሯል። ነገርግን የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው በዋልያው አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በውድድሩ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ያሳካው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል። ተጋባዧ ሀገር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ የውድድሩን ስምንተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ያጋሩ