የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 2-1 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ ከተደረገው ጨዋታ በኋላ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሠልጣኝ ለድህረ-ጨዋታ አስተያየት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ብቻ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ውበቱ አባተ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

ስለጨዋታው

ይህ አራተኛ ጨዋታችን ነው። ከዚህ ቀደም ከኤርትራ እና ከብሩንዲ ጋር ነጥብ ተጋርታናል በመጨረሻው የኤርትራ ጨዋታም እኩል ወጥተን በመለያ ምት ነው የተለያየነው። ደረጃ በደረጃ በቡድን ክፍሉ መሻሻሎች አሉ። በዛሬው ጨዋታ በሁለት ግቦች መምራት ከቻልን በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል። ሆኖም አንድ ግብ ተቆጥሮብን 2-1 አጠናቀናል። ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነበር የኮንጎ ቡድን በአካል ብቃት ላይ መሰረት ያደረገ ቡድን ነው። ያንን ተቆጣጥረን የማሸነፍ ዕድሉን አግኝተናል።

ቡድኑ ስለያዘው የሰባተኛ ደረጃ

እኔ በውድድሩ ላይም ጥያቄ አለኝ። በሦስት ምድቦች ዘጠኝ ቡድኖች ነበርን። ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ብቻ ነው ያደረግነው። ከዛ ይልቅ በሁለት ምድብ አራት እና አምስት ቡድኖች ቢደለደሉ የተሻለ ነበር። ያ ለቡድኖቹ በየምድባቸው ሦስት እና አራት ጨዋታዎችን የማድረግ ዕድል ይሰጥ ነበር። የአሁኑን የውድድሩን አካሄድ ስናይ በደረጃ ሰባተኛ እና ስምንተኛ የሚኖርበት ቢሆንም በሜዳ ላይ ብቃት ግን በቡድናችን ደስተኛ ነን። ከቡድናችን ጥሩ መጫወት አንፃርም ሰባተኛ ነን ማለት አንችልም።

በሁለቱ አጋማሾች ስለነበረው የቡድኑ የዕለቱ ብቃት

በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ነበረን። ወደ ግብ በመድረስ እና ዕድሎችን በመፍጠርም የተሻልን ነበርን። እንደውም ካገባናቸው ግቦች በላይ የሆኑ ዕድሎችን መፍጠር ችለናል። ከሌላው ጊዜ በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ የተሻልን ነበርን። በመጀመሪያው የኤርትራ ጨዋታ ሦስት ጊዜ መርተን ነው አቻ የወጣነው። በብሩንዲው ጨዋታም መርተን ነው አቻ የተለያየነው። በተለይ በብሩንዲው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ቡድናችን ወደ ኋላ አፈግፍጎ ነበር። ያ በራስ ከመተማመን ጋር የተያያዘ ነው የሚመስለኝ። ተደጋጋሚ ጨዋታዎች በተደረጉ ቁጥር ይህንን መቅረፍ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። እንደ አጠቃላይ በብዙ መልኩ የተሻለ ነገር ነው የነበረን። ነገር ግን ሁለት ጎል አግብተን ከመቅደማችን አንፃር ያለፉትን ጨዋታዎች እየመሩ ነጥብ ከመጋራቱ አኳያም ቡድናችን ከዕረፍት መልስ ወደ ኋላ በማፈግፈግ መንገድ ነው የሄድነው። ያ ቢሆንም የኳስ ቁጥጥሩ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ባይሆንም ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረግነው ነገር ጥሩ ነበር። በሁሉም መልክ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የነበረውን ተፅህኖ ተቋቁመን አሸንፈን መውጣት ችለናል።

ስለቡድኑ የውድድሩ ቆይታ

የእኛ ብሔራዊ ቡድን ወደዚህ ውድድር ሲገባ በቀጣይ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መጋቢ የሚሆኑ ወጣት ተጫዋቾችን ለማፍራት ነው። ሁለተኛ ልምድ ለማግኘት እና የአካባቢው ቡድኖች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለማየት ነው። ጎን ለጎን ደግሞ አዘጋጅ እንደመሆናችንም ውጤታማ ነገር ለመስራት ነው። ከውጤት ጋር ተያይዞ በፈለግነው ደረጃ አሳክተነዋል ማለት አይቻልም። በኤርትራ ከመለያ ምት ከመሸነፋችን ውጪ ሁለት አቻ ወጥተን አንድ ነው የተሸነፍነው። ከዛ አንፃር ሲታይ ብዙ የሚያስደስት አይደለም። ነገር ግን ከገባንበት ዓላማ አንፃር ጥሩ ቡድን እንዳለን ቀጣይ ለምንሰራው ሥራ በየቦታው ምትክ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለማፍራት ጥረት እያደረግን እንደሆነ አይቻለሁ። ዋናው ቡድን ላይ ያለው የእንቅስቃሴ ብልጫ በዚህ በወጣት ቡድኑ ላይም በእያንዳንዱ ጨዋታ መመልከት ችለናል። ከዛ አንፃር ለእኛ ትልቅ ጥቅም ነበረው። እንደ ክፍተት ያየሁት ምንአልባት ቡድኑ ዝግጅት ሲያደርግ ራሳችንን በወዳጅነት ጨዋታ ከማየት አንፃር ከፍተኛ ክፍተት ነበረብን። ያን ባለማድረጋችን ውድድር ውስጥ ከገባን በኋላ ነበር ቡድኑን ለመገንባት ስንሞክር የነበረው። ወደ ፊት እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ማግኘት ከቻልን ቡድኑን ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደሚቻል ተስፋ አድርጋለሁ። በሌላ በኩል ቅድም እንዳልኩት ያልተመቸኝ ነገር የውድድሩ አካሄድ ነው። ጠንካራ ቡድኖችን ለመለየት ያስቸግራል። እንደ ዩጋንዳ ዓይነት ጠንካራ በድን የሚጫወተው ለደረጃ ነው። ዲሞክራቲክ ኮንጎም ጠንካራ በድን ነው ፤ ሌሎችም እንደዛው። በሁለት ምድብ ቢሆን በትክክለኛ ብቃት ወደ ቀጣዩ ደረጃ ማለፍ ይቻል ነበር ብዬ ነው የማስበው። ይህንን በቀጣይ ሴካፋ ሊያስተካክለው ይችላል። በተረፈ ግን ጥሩ ልምድ አግኝተንበታል።

ስለቡድኑ አጨዋወት

አሁን ቢያንስ አንድ የተጨበጠ ነገር ይዘናል። ‘ቡድኑ ይህንን ይመስላል’ የሚለውን ነገር እኛ ሳንሆን ተጋጣሚዎች እና ባለሙያዎች ጭምር የመሰከሩት ነገር ነው። ይህንን እንደ ሀገር ማስፈን መቻላችን አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ትርጉም የሌለው ቅብብል ብቻ ሳይሆን ወደ ግብ የሚያድግ የቅብብል ብልጫ እንዲኖረን ደግሞ ይበልጥ መስራት አለብን። ለዛም ነው እየሰራን ያላነው። እንደታየው በየጨዋታዎቹ ጎል ማስቆጠር እና ብልጫ መውሰድ ችለናል ፤ ይህንንም ለማሳደግ ጥረት እናደርጋለን። ከተጋጣሚዎቻችን አንፃር ያየነው በራሳችን መስራት የሚገባን ክፍተት አለ ብዬ የወሰድኩት ከአካል ብቃት ዝግጁነት አንፃር ያለው ልዩነት ነው። ምን አልባት እንደ ብሩንዲ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ግዙፎች ላንሆን እንችላለን። ግን በራሳችን መጠን ጠንካራ መሆን እንዳለብን እና ከተጋጣሚ የሚመጣን ጫና ለመቋቀም መስራት እንዳለብን ተምሪያለሁ። ይህንን ተጫዋቾቹም ያዩት ይመስለኛል። አንዳንዴ ‘ከዚህ ጨዋታ ተርፈው ይወጣሉ ወይ ?’ በሚያስብል ደረጃ ግጭቶች ከባድ ነበሩ። እዛ ላይ መስራት ከቻልን የሚቀሩንን ነገሮች እያሻሻልን ቡድኑን እንገነባለን ብዬ አስባለሁ። በአንድ ነገር ግን ደስተኛ ነኝ ቢያንስ ‘ይህ ቡድን እንደዚህ ነው’ ተብሎ ከማይታወቅ ነገር ወደ የሚታወቅ ነገር መምጣት በራሱ አንድ ዕድገት ነው ብዬ ነው ብዬ ነው የማስበው።

በቡድኑ ዙሪያ ስላላቸው ዕቅድ

እንደ ዕቅድ ዋናው ፍላጎታችን ይህ ቡድን የዋናውን ቡድን ክፍተቶች ለመሽሸፈን ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ማፍራት ነው። ከዛ አንፃር እንደገና ሌላ ሴካፋ እስኪመጣ መጠበቅ አለበት ብዬ አላስብም። በተለያየ ጊዜ በወዳጅነት ጨዋታ እየተገናኙ ይህንን ነገር ማስቀጠል እንዳለብን ይሰማኛን። ከዛ ውጪ እዚህ ያየናቸውን ወደ ዋናው ቡድን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለተወሰኑት ዕድሉን በመስጠት የተጀመረውን ሥራ ለማስቀጠል እንሞክራለን።