ድሬዳዋ ከተማ ጋናዊ ተጫዋች ለማስፈረም ስምምነት ላይ ደርሷል

በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ግዙፉን የመስመር ተጫዋች ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር አስረኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማ የአሠልጣኙን ውል ካራዘመ በኋላ በዝውውር ገበያው ላይ በንቃት በመሳተፍ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል። ለከርሞው ተጠናክሮ ለመቅረብ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ክለቡም በዛሬው ዕለት ጋናዊውን የመስመር ተጫዋች አብዱለጢፍ መሐመድ የግሉ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሷል።

2010 ላይ ሲዳማ ቡናን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አብዱለጢፍ አንድ ዓመት በሲዳማ ቡና ከተጫወተ በኋላ ወደ ሀገሩ መመለሱ አይዘነጋም። በተሰረዘው የውድድር ዘመን (2012) ደግሞ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጎራ በማለት ለስሑል ሽረ ሲጫወት የነበረ ሲሆን አሁን ዳግም ሦስተኛ የኢትዮጵያ ክለብ ለማግኘት መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከአብዱለጢፍ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው ክለቡ ሁለቱን ወሳኝ ተከላካዮቹ ፍሬዘር ካሳ እና በረከት ሳሙኤልን በቅርቡ ማጣቱ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም የተጫዋቾቹን ምትክ ለማግኘት አንድ ሌላ የውጪ ዜግነት ያለው ተከላካይ ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።