ጅማ አባጅፋር የረዳት አሰልጣኞቹን ውል አራዘመ

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በቅርቡ የሾመው ጅማ አባ ጅፋር አሁን ደግሞ የምክትል አሰልጣኙን እና የግብጠባቂዎች አሰልጣኙን ውል አራዝመዋል።

ጅማ አባ ጅፋር በ2014 የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ እራሱን በማጠናከር የተሻለ ቡድን ለመሆን ወደ እንቅስቃሴ የገባው አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በመሾም ነበር። አሁን ደግሞ ያለፉትን አራት ዓመታት ከተለያዮ አሠልጣኞች ጋር ምክትል አሰልጣኝ በመሆን የሰራው እና አንዳንዴም ቡድኑን በጊዜዊ አሰልጣኝነት ሲመራ የምናቀው የሱፍ ዓሊ ከጅማ አባጅፋር ጋር ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆየውን አዲስ የውል ስምምነት ፈፅሟል።

ሌላው በጠንካራ ባለሙያነቱ የሚታወቀው እና ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ የቻሉትን ሠዒድ ሀብታሙን እና አቡበከር ኑሪን ከታችኛው ሊግ በማምጣት ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ የሚታወቀው የግብጠባቂዎች አሠልጣኙ መሐመድ ከአባጅፋሮች ጋር የሚያቆየውን አዲስ ውል መፈረሙ ታውቋል። በነገራችን ላይ መሐመድ የክለቡ የሰርቪስ ሹፌር በመሆን በማገልገል ሁለገብነቱን ሲያሳይ መቆየቱ ይታወሳል።

በሌላ ዜና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ አንድ ምክትል አሠልጣኝ በቅርቡ እንደሚቀጥሩ ሲጠበቅ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ክለቡ የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደሚያስተዋውቁ ይጠበቃል።